ድሬዳዋ ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሚኪያስ ግርማን ለማስፈረም ከስምምነት መድረሱ ታውቋል።
በክረምቱ ዮሀንስ ሳህሌን አሰልጣኝ አድርጎ በመቅጠር አንድ ግብ ጠባቂ እና የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ማስፈረም የቻለው ድሬዳዋ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ አማካይ ስፍራ በማዞር ሚኪያስ ግርማን አስፈርሟል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን የተገኘው ሚኪያስ አራዳ ክ/ከተማን ለቆ በ2009 አጋማሽ ወደ ባህር ዳር ከተማ ካመራ በኋላ ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ መርዳትም ችሏል። ወደ ታይላንድ በማቅናትም በታሂ ሊግ 1 በሚወዳደረው ቻይናት ሆርንቢል የሙከራ ጊዜ አሳልፎ መመለሱ የሚታወስ ነው። በክለቡ ጥሩ የሙከራ ጊዜ ቢያሳልፍም የውጪ ተጫዋቾች ኮታ በመሙላቱ ምክንያት ኮንትራት ሳይፈርም መቅረቱም አይዘነጋም።
በአንድ ዓመት ኮንትራት ለብርቱካናማ ለባሾቹ ለመጫወት የተስማማው ሚኪያስ በድጋሚ ወደ ታይላንዱ ክለብ የመጓዝ እድል የሚያገኝ ከሆነ የመሄድ መብት እንዳለው ተገልጿል።