የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2010 ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ ሲደረግ የፕሬዝዳንት ምርጫ እና የስራ አስፈፃሚ ማሟያ ምርጫውንም አከናውኗል።
በኢትዮጵያ ሆቴል ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ በተደረገው ጉባዔ የ2009 ቃለ ጉባኤን ማቅረብ እና ማፅደቅ፣ የ2010 የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ማቅረብ እና ማፅደቅ፣ የ2010 የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ እና ማፅደቅ፣ የ2011 እቅድ ማቅረብ እና ማፅደቅ፣ ተሻሽሎ የቀረበውን የፌዴሬሽኑን ደንብ ማቅረብ እና ማፅደቅ እንዲሁም የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ሟሟያ ምርጫ ማካሄድ ተብለው በተቀመጡ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ምልዓተ ጉባዔው በደንቡ መሰረት መሞላቱን በማረጋገጥ የተጀመረው ጉባዔው በእለቱ በተገኙት የክብር እንግዳ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሯል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ኃይለሰማያት መርሃጥበብ ጉባዔው በይፋ መጀመሩን የማብሰሪያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ ስላለው ማዘውተሪያ ቦታዎች እጥረት ሃሳባቸውን አካፍለዋል። “እኔ ወደ ቦታው ስመጣ ገና ሁለት ሳምንት አልሞላኝም። ነገር ግን እኔ ወደ ቢሮው ከመጣው በኋላ በጥሩ መነሳሳት እየሰራን ነው። ከተማችን ውስጥ በርካታ ወጣቶች አሉ ነገር ግን እነዚህ ወጣቶች ስፖርት መስራት ቢፈልጉ እና እግር ኳስ መጫወት ቢያቹ ማዘውተሪያ ቦታ ስለሌለ ወደ አልባሌ ቦታ ይሄዳሉ። በስፖርቱ የአዲስ አበባ ችግር ደግሞ ይህ የማዘውተሪያ ቦታ ነው። ስፖርቱን በዜና በወሬ ብቻ ወጣቱ ከሚሰማው ያለውን አቅም አውጥቶ እንዲጠቀም ከተማ መስተዳደራችን ከፍተኛ እቅዶችን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።” በማለት የነሱ ቢሮ በማዘውተሪያ ቦታዎች እና በፖሊሲዎች ዙርያ የፈለገው አካል ወደ እነሱ በመጠጋት ስራዎችን አብረው መስራት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ከክብር እንግዳው ንግግር በኋላ የፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ መድረኩን በመረከብ አጀንዳዎቹን ያስተዋወቁ ሲሆን ከተሳታፊ ተጨማሪ አጀንዳ ይያዝ የሚል ጥያቄ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል። በመጀመሪያ የ2010 የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይ አምና እንደ እቅድ ተይዘው ሳይሰሩ የቀሩ ሃሳቦች ላይ ነጥቦች ተነስተዋል።
በአፈፃፀም ሪፖርቱ ስለ ሲቲ ካፕ፣ ስለ ዲቪዚየኖች ውድድር፣ የማዘውተሪያ ቦታ፣ የቴክኒክ ጉዳዮች እና የመሳሰሉት ላይ ከጉባዔው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተሰተው ውይይት ተደርጓበት መሻሻል አለባቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ አደራ ተሰቶ በመተማመን እንዲፀድቅ ተደርጓል። ከአፈፃፀም ሪፖርቱ በመቀጠል የ2010 የኦዲት ሪፖርት በአቶ ሚካኤል አማካኝነት ቀርቦ ጉባዔው ውይይት አድርጓበት በማፀደቅ ለምሳ ጉባዔው እንዲበተን ተደርጓል።
ከምሳ መልስ በዋናነት የ2011 እቅድ እና የተሻሻለው የፌደሬሽኑ ደንብ ላይ የመከራከሪያ ነጥቦች ከተለያዩ ወገኖች ቀርበው ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። በተለይ ከአምስት አመታት በፊት ስራ ላይ የዋለውን የፌዴሬሽኑን ደንብ እንዲሻሻል በቀረበው አጀንዳ ዙሪያ ከጉባዔው በርካታ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ እና ምላሽ እንዲሰጥባቸው ተደርጓል።
በመቀጠል የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ የሟሟያ ምርጫው የተከናወነ ሲሆን ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት ምርጫውን በአስመራጭነት የሚመሩ ገለልተኛ አካላት ከጉባዔው የመምረጥ ድርጊት ተከናውኗል። ሶስት ገለልተኛ አስመራጮችን ከተመረጡ በኃላ ለፕሬዝዳንትነትም ለስራ አስፈፃሚነትም የሚወዳደሩ እጩ አካላት እራሳቸው እንዲያስተዋውቁ እና ስለሚሰሯቸው ስራዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል። ለፕሬዝዳንትነት ከሚወዳደሩት ሶስት እጩዎች አቶ አብዱልፈታ ተስፉ ባልታወቀ ምክንያት በቦታው ሳይገኙ በመቅረታቸው በቀጥታ ከውድድሩ ውጪ እንዲሆኑ እና በቦታው የተገኙት ሁለቱ ብቻ እንዲወዳደሩ የተደረገ ሲሆን ለስራ አስፈፃሚነት ከሚወዳደሩት 16 ግለሰቦች ኢ/ር የማታወርቅ አበበ እና አቶ ኤፍሬም ግዛው ባለተገለፀ ምክንያት እንዲሁም አቶ አስራት ሀይሌ እና አቶ ምትኩ መኩሪያ ከምርጫው ራሳቸውን በማግለላቸው ከእጩነት እንዲሰረዙ ተደርጓል።
በዚህ ስነስርዓት ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት እጩዎች በተፈቀደላቸው ሶስት ደቂቃ ሊሰሩ ስላሰቧቸው እቅዶች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ ሁለቱም ግለሰቦች የውድድር ፎርማትን ስለማስተካከል እና በውድድር ላይ ተሳታፊ ስለሚሆኑ ክለቦች የአቅም ውስንነት ችግር መፍትሄ አለን በማለት ገለፃ አድርገዋል።
በመቀጠል በቀጥታ ወደ ድምፅ አሰጣጥ ስነስርዓት የታለፈ ሲሆን ድምፅ መስጠት ከሚገባቸው 43 ድምፅ ሰጪዎች 35ቱ በመገኘታቸው ምርጫው እንዲከናወን ተደርጓል።
በምርጫውም መሰረት ኢ/ር ሀይለየሱስ ፍስሃ በ20 ድምፅ አቶ ተስፋዬ ካሳይን በስምንት ድንፇች በመብለጥ አሸናፊ መሆናቸው እና አዲሱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ተረጋግጧል። በስራ አስፈፃሚ የሟሟያ ምርጫው ድምፅ መሰረት ደግሞ አራት ግለሰቦች ተመርጠዋል። ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ(18)፣ ዶ/ር አይናለም አባይነህ(17)፣ አቶ የኔነህ በቀለ(15)፣ አቶ ነጋሴ ሀለፉ(14) አዲሶቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት መሆናቸው በድምፁ መሰረት ተረጋግጧል።
ከምሳ ሰዓት በፊት በነበረው ውይይት ተጨማሪ አጀንዳ ይያዝ የሚል ሃሳብ ከጠቅላላ ጉባኤው በመነሳቱ ይህም ደግሞ የፌዴሬሽኑን ምክትል ፕሬዝዳንት ጠቅላላ ገባዔው ይምረጥ በተባለው መሰረት አዲሶቹ የስራ አስፈፃሚ እና ነባሮቹ የስራ አስፈፃሚዎች በምክትልነት መወዳደር እንደሚፈልጉ ጥያቄ ቀርቦላቸው ወደ ድምፅ አሰጣት ታልፏል። በዚህም መሰረት ምክትልነት እንፈልጋለን ብለው ከተወዳደሩት ዶ/ር ዘላለም፣ አቶ በለጠ እና አቶ የኔነህ አቶ በለጠ ዘውዴ በ24 ድምፅ በማሸነፋቸው የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
በስተመጨረሻ አዲሱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ኃይለየሱስ ፍስሃ ስለመረጡዋቸው ምስጋና አቅረበው ይህንን ብለዋል። “በመጀመሪያ አዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽንን በደንብ ይመራል ብላችሁ እና አምናችሁ ስለመረጣችሁኝ ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለው። ጥሩ እቅድ አቅርቤ እቅዴንም በአግባቡ ከምትጠብቁት በላይ ሰርቼ ላስደስታችሁ ስራዎችን እሰራለው” ብለዋል።