ኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን ለነገው የማጣርያ ጨዋታ ተዘጋጅተዋል

በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከጋና፣ ኬንያ እና ሴራሊዮን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው እለት ሁለተኛ የማጣርያ ጨዋታውን ሀዋሳ ስታድየም ላይ ያከናውናል። 

ዋልያዎቹ ከነሀሴ ሶስት ጀምሮ በሀዋሳ ከትመው ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ሰኞ እለት የተጫዋቾች ቁጥር ወደ 23 ተቀንሰው ልምምዳቸውን ቀጥለዋል። በዛሬው እለትም ረፋድ 4:00 ላይ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም አከናውነዋል። 32 ያህል ደቂቃዎች በፈጀው የልምምድ መርሐ ግብርም ቀለል ያሉ ከኳስ ጋር የተያያዙ ስራዎች ስርተዋል።

ከማክሰኞ ጀምሮ በሀዋሳ ልምምዱን እያደረገ የሚገኘው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድንም በተመሳሳይ በዛሬው እለት ሁለት ጊዜ ልምምድ ያከናወነ ሲሆን በቆሙ ኳሶች ላይ ያተኮረ ስራ ሲሰሩ ተስተውለዋል። 

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የሚመሩት ቱኒዚያዊው ሳዶክ ሴሌሚ፣ ረዳቶቹ ሊቢያዊው አቲያ አምሳድ እና ቱኒዚያዊው አይመን ኢስማይል እንዲሁም ቱኒዚያዊው አራተኛ ዳኛ ነስረላህ ጃኦዋዲ ከነገው ጨዋታ በፊት ልምምዳቸውን በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም 09:00 ላይ ሰርተዋል። 

የነገ 10 ሰዓቱ የማጣርያ ጨዋታ የሚደረግበት የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም የመግቢያ ዋጋዎች ይፋ የተደረጉ ሲሆን እንደየደረጃቸው 10 ብር፣ 50 ብር እና 100 ብር ይከፈልባቸዋል። በስታድየሙ የተገጠመው ስክሪን በነገው እለት አገልግሎት እንደሚሰጥም ይጠበቃል። በቀጥታ ስርጭት በኩል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ቻነል የሚያስተላልፍ ሲሆን የደቡብ ቴሌቪዥንም ፍቃድ ካገኘ እንደሚያስተላልፈው ተነግሯል።