የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው እለት 2ኛ የምድብ ማጣርያ ጨዋታውን ከሴራሊዮን ጋር ሀዋሳ ላይ ያከናውናል። ከኢትዮጵያ ውጪ ሶስቱ ሀገራት እኩል ሶስት ነጥቦችን የያዙ በመሆኑ ዋልያዎቹ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ሆኗል።
ብሔራዊ ቡድኑ ለሴራሊዮኑ ጨዋታ ከጠራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነውና ዘንድሮ ልዩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው አማኑኤል ዮሀንስ ለመጀመርያ ጊዜ ለዋልያዎቹ የነጥብ ጨዋታ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ተጫዋቹ ስለ ነገው ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ።
ከሶስት ሳምንት በላይ ሀዋሳ ዝግጅት ስታደርጉ ነበር። በአጠቃላይ ዝግጅታችሁ ምን ይመስል ነበር?
ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነበር። ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን ነው። ለብሄራዊ ቡድን ስመረጥ የመጀመሪያዬ ነው፤ ነገር ግን ያሉትን ነገሮች ስመለከታቸው በጣም አሪፍ ናቸው። ከአሰልጣኞቹም ጋር ሆነ ከሁሉም ተጫዋቾች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን።
አንደሚታወቀው ቡድኑ በጋና አስከፊ ሽንፈት ተሸንፏል። ከዚህ አንፃር ቡድኑ ውስጥ ያለው መንፈስ ምን ይመስላል? ከነገው ጨዋታ ምን እንጠብቅ?
አዎ ከሽንፈት ነው የመጣነው። ነገር ግን በዝግጅት ጊዜያችን ከዋናው የሜዳ ላይ ስልጠና ውጪ የክፍል ውስጥ የሳይኮሎጂ ትምህርቶች ሲሰጡን ነበር። ይህ ደግሞ የሆነው ያንን አስከፊ ሽንፈት እንድንረሳው ነው። አሁን ቡድኑ እንደ አዲስ ነው የተዋቀረው፣ ያለንም አሰልጣኝ በጣም ጥሩ አሰልጣኝ ነው። በተጨማሪም ያሉንን ክፍተቶች በአቋም መፈተሻ ጨዋታ አይተናል። ስለዚህ በነገው ጨዋታ ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለው። ዋና አላማችን ለአፍሪካ ዋንጫው ማለፍ ነው። ይህ ደግሞ እንዲሆን ያለ ምንም ምርጫ የነገውን ጨዋታ ማሸንፍ ነው ያለብን። ሁሉም ተጨዋቾች ጋር ያለው ስሜትም ተመሳሳይ ነው ነው። ስለዚህ ከፈጣሪ ጋር የነገውን ጨዋታ እናሸንፋለን ብዬ አስባለው።
በቡሄራዊ ቡድን ጥሪ ሲቀርብልህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። ምን ተሰማህ?
በቡሄራዊ ቡድን ደረጃ ጥሪ ሲቀርብልኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከመምጣቴ በፊት እና ከመጣሁ በኋላ ያለው ነገር በጣም የተለያየ ነው። ነገር ግን በብሩንዲው ጨዋታ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክሬያለው። ይህ ደግሞ የሆነው በቡድን ጓደኞቼ እርዳታ እና አሰልጣኙ የሚከተሉት የጨዋታ ፍልስፍና ከእኔ ፍላጎት ጋር በመጣጣሙ ነው። በተለይ ቡድኑ ውስጥ ያሉት ሲኒየር ተጨዋቾች አዲስነት እንዳይሰማኝ አድርገዋል፤ እነሱንም ላመሰግን እወዳለው።
በኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ጊዜ አሳልፈሀል። አመዛኞቹን ጨዋታዎችም አምበልም ነበርክ። ለብሔራዊ ቡድን ስትመጣ እንዴት አገኘኸው? ከክለብስ በምን ተለየብህ?
በሁለቱ መካከል ልዩነት አለሁ። የክለብ አላማ ተጨዋችን ለብሔራዊ ቡድን ማብቃት ነው። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጽያ ቡናን አመስግናለሁ። ለዚህ ያበቃኝ ክለቤ ነው።
በመጨረሻ የምትለው ካለህ…
ህዝቡ ኳስ ወዳጅ ነው። ነገር ግን የሚገባቸውን አልሰጠናቸውም። የባለፈውን ረስተን የተለመደውን ድጋፋቸውን እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን። ደግሞም ያደርጉልናል።