በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 6 ተደልድሎ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሴራሊዮንን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ዓመቱን በድል ቋጭቷል። በምድቡ የሚገኙት ሁሉም ቡድኖች እኩል ሶስት ነጥቦች መያዛቸውም ምድቡን በውጥረት የተሞላ አድርጎታል።
የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ባለፈው እሁድ በወዳጅነት ጨዋታ ከተጠቀሙት ስብስብ መካከል በመሐል ተከላካይ ስፍራ በጉዳት ከቡድኑ ውጪ በሆነው ሰላሀዲን በርጌቾ ምትክ አንተነህ ተስፋዬን ሲጠቀሙ በአማካይ ስፍራ ከውጪ ሀገራት ክለቦች የተመረጡት እና በወዳጅነት ጨዋታው ያልተሰለፉት ጋቶች፣ ዑመድ፣ ቢኒያም እና ሽመልስ በቀለ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ተካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ዋልያዎቹ በጨዋታው ሙሉውን ክፍለ ጊዜ የኳስ ቁጥጥር እና የሙከራ ብልጫን መውሰድ ችለዋል። ዑመድ ኡኩሪ በሳጥኑ ቀኝ በኩል ወደ ግብ የመታው ኳስ የውጪኛውን መረብ ታኮ ወጥቷል። በ6ኛው ደቂቃ ዑመድ ኡኩሪ በቀኝ መስመር በኩል ጥሩ የግብ እድል ሊፈጥርበት የሚችልበትን ኳስ አግኝቶ በቀጥታ በመምታት መረቡን ታኮ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ የመጀመርያ የግብ አጋጣሚን ከፈጠሩ በኋላ ዋልያዎቹ በሴራሊዮን የሜዳ አጋማሽ በማመዘን ቢጫወቱም በማጥቃት ወረዳው የነበራቸው የቅብብል ስኬት እና ስልነት ዝቅተኛ ሆኖ ታይቷል። በዚህም ምክንያት የጠራ የግብ እድል ሳንመለከት ከግማሽ ሰዓት በላይ ለመጠበቅ ተገደናል።
በ36ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቢንያም በላይ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ የግራ መስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ በጥሩ ሁኔታ የፊት ለፊት ሩጫ አድርጎ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል በመግባት ለማለፍ ሲሞክር በሜዶ ካማራ በመጠለፉ የፍፁም ቅጣት ምት ለኢትዮጵያ ተሰጥቷል። አምበሉ ጌታነህ ከበደም ለግብ ጠባቂው ዞምቦ ሞሪስ የሚወድቅበትን አቅጣጫ የሚወስንበትን እድል ሳይሰጠው ወደ ግብነት በመቀየር ዋልያዎቹን ቀዳሚ አድርጓል። የመጀመርያው አጋማሽ በዚህ መልኩ ተጨማሪ ክስተት ሳንመለከትበት ነበር በኢትዮጵያውያ መሪነት የተጠናቀቀው።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያው ሁሉ የኢትዮጵያ የበላይነት ታይቶበታል። በተለይም የሴራሊዮን ተከላካዮች በሚፈጥሩት የቅብብል ስህተት የግብ መጠኑን ለማስፋት የሚያስችሉ እድሎች ቢፈጠሩም ሳይሳኩ ቀርተዋል። በ57ኛው ጌታነህ ከበደ ጀርባውን ለተከላካዮች ሰጥቶ ኳሱን ከተቀበለ በኋላ በጥሩ ሁኔታ በመዞር ከርቀት የመታው ኳስ ወደ ውጪ የወጣት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ ሲሆን ተቀይሮ የገባው አቤል ያለው ከመስመር እየገፋ ወደ ውስጥ በመግባት ያሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ቢንያም ከማግኘቱ ቀድሞ የሴራሊዮን ተከላካይ ዴቪድ ሲምቦ ተንሸራቶ ያወጣበት ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነው። በ78ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከሴራሊዮን ተከላካዮች የነጠቀውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ በመጠጋት ከግብ ጠባቂው ቅርብ ርቀት በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ የግራ ቋሚውን ለትማ የተመለሰችበት ኳስም የኢትዮጵያን መሪነት ልታሰፋ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።
እንግዶቹ ሴራሊዮኖች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአቻነት ጎል ለማግኘት መጠነኛ ጫና ከመፍጠራቸው ውጪ እምብዛም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈተና የሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። በፊት መስመር የሚገኙት ተጫዋቾች በማጥቃት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ተከላካዮች በቁጥር ከመበላጣቸው በተጨማሪም አንድ ከአስቻለው እና አንተነህ ጋር አንድ ለአንድ በሚገናኙባቸው አጋጣሚዎችም የበላይነት ለመውሰድ ተቸግረው ውለዋልጰ በ67ኛው ደቂቃ ከማዕዘን በተሻማ ኳስ አስደንጋጭ የግብ እድል ፈጥረው በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተፈጠረ ትርምስ ከጎሉ አካባቢ ከራቀው ኳስ ውጪም የሚጠቀስና ግልፅ የሆነ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም።
ጨዋታው በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ 1-0 መጠናቀቁን ተከትሎ ሁሉም የምድቡ ተፋላሚዎች ተመሳሳይ ሶስት ነጥቦችን በመያዝ ተናንቀዋል። ጋና በአራት የጎል ልዩነት ምድቡን ስትመራ ሴራሊዮን ሁለተኛ፣ ኬንያ ሶስተኛ፣ ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል።