በኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨለማ የውድድር ዓመት ውስጥ በግሉ ያንፀባረቀው ካሉሻ ወደ ቡናማዎቹ ቤት ማምራቱ እርግጥ ሆኗል።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ እና ጥሩ ጊዜን ካሳለፉ ተጨዋቾች መካከል አልሃሰን ካሉሻ ዋነኛው ነበር። ተጨዋቹ ምንም እንኳን ቡድኑ ከሊጉ ለመውረድ ቢገደድም በኢትዮ ኤሌክትሪክ መለያ ከአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ጀምሮ እስከ ፕሪምየር ሊጉ ፍፃሜ ድረስ በወጥነት ማገልገል ችሏል። በኤሌክትሪክ ቤት በመስመር አማካይነት በመጫወት የጀመረው ካሉሻ በሂደት የቡድኑ ዋነኛ የጨዋታ አቀጣጣይ መሆን ከመቻሉም በላይ 13 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ጋናዊው አማካይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የአንድ ዓመት ውል ይቀረው ስለነበር በከፍተኛ ሊግ ይቀጥላል ወይስ አይናቸው ያረፈበት የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ይወስዱታል የሚለው ጥያቄ ሲያነጋግር ቆይቷል። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ቡና ከተጨዋቹ ጋር እንደተስማማ እና በኢትዮኤሌክትሪክ ያለውን የውል ማፍረሻ በመክፈል ከቡድኑ ጋር ሊቀላቅለው ከስምምነት መድረሱ ተስመቷል። በርካታ ተጨዋቾቹን የለቀቀው ኢትዮጵያ ቡና አማካይ ክፍሉ ላይ ሁነኛ ተጨዋች ያስፈልገው የነበረ በመሆኑ ካሉሻን ማግኘቱ ለአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የቡድን ግንባታ እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን መናገር ይቻላል። አማካዩ ከቡናማዎቹ ጋር ለሁለት የውድድር ዓመታትን ለመቆየት ሲሆን የተስማማው በቀጣዩ ረቡዕም በፌዴሬሽን ተገኝቶ ፊርማውን በይፋ እንደሚያኖር ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቡና ከዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ኢስማኤል ዋቴንጋ ጋር ባሳላፍነው ሳምንት መጨረሻ መስማማቱ የሚታወስ ነው።