እንኳን ለ2011 አደረሳችሁ!
በኢትዮጵያ እና አፍሪካ በ2011 አበይት እግርኳሳዊ ክንውኖች ይጠበቃሉ። በዓመቱ እግርኳሳችንን ለመከታተል እንዲያመቻችሁ ዋና ዋናዎቹን ክንውኖች ከዚህ በታች ተመልክተናቸዋል።
መስከረም
* መስከረም 6 የኢቢሲ የ2010 የውድድር ዘመን ኮከቦች ምርጫ ይካሄዳል። በእግርኳስ እና አትሌቲክስ በሁለቱም ፆታ ለአሸናፊዎች ሽልማት ይሰጣል።
* በዚህ ወር መጀመርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል። የ2010 ሪፖርት እና የ2011 የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት የስብሰባው አካል ናቸው።
* የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የኮከቦች ምርጫ በዚህ ወር ይጠበቃል። በፌዴሬሽኑ ስር የሚከናወኑት 7 ሊጎች ኮከብ ተጫዋቾች፣ ግብ አስቆጣሪዎች፣ አሰልጣኞች፣ ምስጉን ዳኞች እና ልዩ ተሸላሚዎች ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
* ከ2010 ወደ 2011 የተሸጋገረው የኢትዮጵያ ዋንጫ አራት ጨዋታዎች በመስከረም ወር ይካሄዳሉ። አንድ የሩብ ፍፃሜ፣ ሁለት የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ። ካፍ በዚህ ዓመት የሚደረጉ የክለብ ውድድሮችን በህዳር ወር የሚጀምር በመሆኑ ሀገራት አሸናፊ ክለቦቻቸውን እስከ መስከረም መጨረሻ ማሳወቅ ስለሚኖርባቸው ጨዋታዎቹ የግድ መስከረም ወር ላይ ይከናወናሉ።
* የቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ እንደሚካሄዱ ይጠበቃል። በክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ የሚደረጉት የተለያዩ ውድድሮች እስከ ጥቅምት የመጀመርያ ሳምንት ድረስ እንደሚዘልቁ ፍንጭ የሚሰጡ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
* መስከረም 30 ቀን 2011 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ሶስተኛ ጨዋታዎች ይቀጥላሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ ኬንያን ይገጥማል።
ጥቅምት
* ጥቅምት 4 ቀን 2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ኬንያ አምርቶ የሀራምቤ ኮከቦችን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አራተኛ የምድብ ጨዋታ ይገጥማል።
* የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በዚህ ወር መጀመርያ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። የሊጉ እና የዋንጫ አሸናፊው የሚገናኙበት ይህ ውድድር በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲዘነጋ እንደመስተዋሉ ላይከናወንም ይችላል።
* የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በወሩ መጀመርያ ሊከናወን ይችላል። በውዝግብ ከተሞላው የምርጫ ሒደት በኋላ አዲሱ ፌዴሬሽን የ2011 እቅዱን እና በጀቱን አንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
* የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወሩ አጋማሽ እንደሚጀምር ይጠበቃል። በ1990 ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ አመዛኙ ውድድር በጥቅምት ወር ከመጀመሩ አንፃር የዘንድሮውም ከዚህ እንደማያልፍ ይጠበቃል።
* የሴቶች እና የወጣት ውድድሮች በዚህ ወር እንደሚጀመሩ ይጠበቃል።
ህዳር
* የካፍ ውድድሮች የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት በዚህ ወር መጀመርያ ላይ ይካሄዳል። በአዲሱ አካሄድ መሠረት የሚካሄደው ይህ ውድድር ኖቬምበር ላይ ጀምሮ ሜይ ወር ላይ የሚጠናቀቅ ይሆናል። የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር (ቻምፒየንስ ሊግ) እና የኢትዮጵያ ዋንጫው አሸናፊ ክለብ (ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) የቅድመ ማጣርያ ተጋጣሚዎቻቸውን የሚያውቁ ይሆናል።
* ህዳር 9 ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አምስተኛ የምድብ ጨዋታ ጋናን በሜዳቸው ያስተናግዳሉ። ጨዋታው የሚደረግበት ቦታ ይፋ ያልተደረገ ሲሆን ቡድኑ ከጋናው ጨዋታ በፊት የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርግበት እድልም አለው።
* የካፍ ውድድሮች የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ህዳር 18 እና 19 ሲካሄዱ የመልስ ጨዋታዎች ኅዳር 25 እና 26 ይከናወናሉ።
* የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ በህዳር ወር አጋማሽ እንደሚጀመሩ ይጠበቃል።
ታኅሳስ
* የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ሴካፋ) በዚህ ወር እንደሚከናወን ይጠበቃል።
* የኢትዮጵያ ክለቦች በካፍ የክለብ ውድድሮች የቅድመ ማጣርያ ተጋጣሚዎቻቸውን ካሸነፉ የአንደኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከታኅሳስ 5-7፣ የመልስ ጨዋታቸውን ደግሞ ከታኅሳስ 12-14 የሚያከናውኑ ይሆናል።
* ክለቦቻችን የአንደኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታቸውን በድል ከተወጡ ወደ ምድብ የሚገቡ ይሆናል። ታኅሳስ 19 የምድብ ድልድል የሚወጣበት ዕለት ነው።
ጥር
* በካፍ የክለብ ውድድሮች 3 የምድብ ጨዋታዎች በጥር ወር ይከናወናሉ።
የካቲት
* በካፍ የክለብ ውድድሮች 3 የምድብ ጨዋታዎች በጥር ወር ይከናወናሉ።
* በመስከረም ወር 2012 ዛምቢያ ሉሳካ ላይ የሚደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ የሚደረጉ የማጣርያ ጨዋታዎች በዚህ ወረ ይጀምራሉ። በወሩ አጋማሽ ላይ የመጀመርያ፣ በወሩ መጨረሻ ደግሞ የመልስ ጨዋታዎች እንደሚከናወኑ ይጠበቃል። ከ23 ዓመት ብሔራዊ ቡድናችን ለ2017 ውድድር ለማለፍ ከሱዳን ጋር ባደረገው የቅድመ ማጠመርያ ጨዋታ በድምር ውጤት ተሸንፎ መውደቁ ይታወሳል።
መጋቢት
* የካፍ ውድድሮች የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ከመጋቢት 6 እስከ 8 ባሉት ጊዜያት ይከናወናሉ።
* የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ከሴራሊዮን ጋር ከመጋቢት 12-15 ባሉት ቀናት ውስጥ ይጫወታል። ከዚህ ጨዋታ በፊት የወዳጅነት ጨዋታ የማድረግ እድል አለው።
* ኢትዮጵያ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የቅድመ ማጣርያ ተጋጣሚዋን ካሸነፈች የአንደኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታዋን በዚህ ወር አጋማሽ ታከናውናለች።
* አንድም የኢትዮጵያ ክለብ አሳክቶት የማያውቀው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታ ከመጋቢት 27 እስከ 29 ባሉት ቀናት ይከናወናል።
ሚያዝያ
* የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የአንደኛ ዙር ማጣርያ የመልስ ጨዋታ በወሩ መጀመርያ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል። ብሔራዊ ቡድኖቻችን (በሁለቱም ፆታዎች) ይህን ዙር ካለፉ ለሉሳካው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የሚያልፉ ይሆናል።
* የካፍ ውድድሮች ሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች ከሚያዝያ 4-6 ባሉት ቀናት ይከናወናል።
* በ2020 በጃፓኗ ቶኪዮ የሚስተናገደው ኦሎምፒክ የእግርኳስ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች የቅድመ ማጣርያ ደርሶ መልስ ጨዋታዎች በዚህ ወር አጋማሽ እና መጨረሻ መደረግ ይጀምራሉ።
* የካፍ ውድድሮች የግማሽ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በተመሳሳይ በሚያዝያ ወር አጋማሽ እና መጨረሻ ይከናወናል።
ግንቦት
* የኦሎምፒክ ማጣርያ የአንደኛ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በግንቦት ወር አጋማሽ እና መጨረሻ ይከናወናሉ።
* የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ደርሶ መልስ ጨዋታዎች በግንቦት ወር አጋማሽ እና መጨረሻ ይደረጋሉ።
* ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሳምንት በግንቦት ወር የመጨረሻ ሳምንት ይኖራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የወዳጅነት ጨዋታ የማድረግ እድል አለው።
* የአፍሪካ ዋንጫ በካሜሩን አስናጋጅነት ግንቦት 30 ይጀመራል። ዋልያዎቹም ከምድብ ማጣርያው ማለፍ ከቻሉ እስከ ሰኔ 23 ድረስ በሚከናወነው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።
ሰኔ
ዓመቱ በአህጉራዊ ውድድሮች የተጨናነቀ ከመሆኑ አንፃር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ በጥሩ ሁኔታ ከተመሩ በዚህ ወር ሊጠናቀቁ ይችላሉ።
ሐምሌ
የኦሎምፒክ ማጣርያ ሁለተኛ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በወሩ አጋማሽ እና መጨረሻ ላይ ይከናወናሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይህን ዙር ከተወጣ በግብፅ አስተናጋጅነት ታኅሳስ 2012 ላይ በሚከናወነው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የሚካፈል ይሆናል። በውድድሩ የፍጻሜ ተፋላሚ ከሆነም ወደ ቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚያልፍ ይሆናል።
ነሀሴ
* ክለቦቻችን በአፍሪካ ውድድር ለውጥ ምክንያት በጊዜ ለ2012 የወድድር ዘመን ቅድመ ዝግጅታቸውን በጊዜ ሊጀምሩ ይችላሉ። ሊጉ በጊዜ ከተጠናቀቀም በሐምሌ መጨረሻ ወይም ነሀሴ መጀመርያ ላይ ዝግጅት ሊጀምሩ ይችላሉ።
* በካታር አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ2022 የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣርያ በዚህ ወር ይጀምራል። ኢትዮጵያ ከነሀሴ መጨረሻ ጀምሮ በሚከናወነው የቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ እንደምትጫወት ይጠበቃል።
* የ2019/20 የአፍሪካ ውድድሮች በዚህ ወር መጨረሸ እንደሚጀምር ይጠበቃል። የ2011 የሀገር ውስጥ ውድድሮች በጊዜ ካልተጠናቀቁ የሊግ እና ዋንጫ አሸናፊዎች ያለ በቂ እረፍት በአፍሪካ ውድድር ላይ ሊካፈሉ ይችላሉ።
ጳጉሜ
* በነሀሴ ወር ላይ እንደተገለፀው በካፍ የክለብ ውድድሮች የቀን ለውጥ አስገዳጅነት ሊጋችን በመስከረም ወር ሊጀመር ይችላል። ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ጳጉሜ ወር የቅድመ ውድድር ጨዋታዎች የሚጠናቀቁበት ወቅት ሊሆን ይችላል።
* በዛምቢያ ሉሳካ የሚከናወነው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ጳጉሜ ወር ላይ ይጀመራል። ዋልያዎቹ እና ሉሲዎቹ ማጣርያውን ካለፉ ለውድድሩ ይቀርባሉ።