ግርማ ታደሰ በደቡብ ፖሊስ ውላቸውን አራዝመዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2010 የውድድር ዓመት አጠቃላይ ቻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ደቡብ ፖሊስ የዋና አሰልጣኙ ግርማ ታደሰን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለማደስ ከስምምነት መድረሱን ክለቡ አስታውቋል። 

አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሀዋሳውን ክለብ የምድብ ለ የበላይ ሆኖ በማጠናቀቅ የምድብ ሀ አሸናፊው ባህር ዳር ከተማን 1-0 በማሸነፍ አጠቃላይ አሸናፊ እንዲሆን የረዱት ሲሆን ክለቡ ከ9 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግም አስችለዋል። አሰልጣኙ ውላቸው በውድድሩ ማብቂያ ላየ የተጠናቀቀ በመሆኑ ቀጣይ ቆይታቸው እርግጥ አለመሆኑን ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፃቸው ይታወሳል። አሁን ግን ከክለቡ ጋር ባደረጉት ድርድር ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው የ2011 የውድድር ዘመንን በክለቡ የሚያሳልፉ ይሆናል። 

በዝውውር መስኮቱ እስካሁን ምንም እንቅሴቃሴ ያላደረገው ደቡብ ፖሊስ ከነገ ጀምሮ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ይፋ እንደሚያደርጉ የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። አሰልጣኝ ግርማ በበኩላቸው በአነስተኛ ወጪ ጠንካራ ቡድን በመገንባት በሊጉ ለመፎካከር እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።