ደደቢት ከመስከረም 15 በፊት ተጫዋቾቹን ለብሄራዊ ቡድን እንደማይለቅ አስታወቀ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለብሄራዊ ቡድን ዝግጅት መስከረም 10 ሁሉም ተጫዋቾች እንዲገኙ ማዘዙን ተከትሎ ደደቢት ተጫዋቾቹን ከተፈቀደው ጊዜ ውጪ እደማይለቅ አስታውቋል፡፡

የደደቢት እግርኳስ ክለብ ህዝብ ግንኙነት አቶ ኪዳኔ ተስፋፅዮን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ክለባቸው ከመመርያው ውጪ የሆነ አሰራር እንደማይቀበል አስታውቀዋል፡፡

‹‹ ብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት የሚደርግበት መንገድ ላይ ቅሬታ አለን፡፡ መስከረም 19 ለሚደረገው ጨዋታ ተጫዋቾችን የጠሩት ለመስከረም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፌዴሬሽኑ ደንብ ጋር ይጣረሳል፡፡ የፌዴሬሽኑ መተዳደርያ ደንብ ክለቦች ተጫዋች እንዲለቁ የሚያዘው ለወዳጅነት ጨዋታ 4 ቀናት ሲቀሩ ፣ ለማጣርያ ጨዋታዎች ደግሞ 10 ቀናት ሲቀረው ነው፡፡ ስለዚህ ከቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ተጫዋቾቻችንን የምንለቀው መስከረም 15 ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

አቶ ኪዳኔ አክለውም የብሄራዊ ቡድኑ አሰራር በዝግጅታቸው ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችን የሚራው በፈለገበት ሰአት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተጫዋቾቻችንን ጉልበት ከመጨረስ ውጪ ጥቅም የለውም፡፡ የቅድመ ውድድር ዝግጅታችን ላይም አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረብን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋቾች መካከል የደደቢቶቹ ታሪክ ጌትነት ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ስዩም ተስፋዬ እና ዳዊት ፍቃዱ መካተታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ያጋሩ