ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይናገራሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሰኔ ወር በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች። ባሳለፍነው እሁድም ሀዋሳ ላይ ሴራሊዮንን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ከሌሎቹ የምድቡ ሀገራት ጋር በነጥብ መስተካከል ችሏል። 

ባለፈው ግንቦት ወር ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆናቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅርብ ናቸው። ቡድኑ ሴራሊዮንን በገጠመበት ጨዋታ ላይም በስታድየም ተገኝተው ጨዋታውን ሲከታተሉ እና ነጥቦችን በማስታወሻቸው ላይ ሲይዙ ተመልክተናቸዋል። 

የቀድሞው የዋልያዎቹ አለቃ በአዲሱ ስራቸው የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታውን ስላደረገው ብሔራዊ ቡድን ያላቸውን እይታ ለሶከር ኢትዮጵያ አካፍለዋል። 

” የአንድ ብሔራዊ ቡድን ጥንካሬ የሚለካው አብሮ በመቆየት እና በመተዋወቅ ሂደት በሚሰሩ ስራዎች በሚያስመዘግበው ውጤት ነው። የኛ ብሔራዊ ቡድን ሲፈለግ ብቻ የሚሰባሰብ ከዛ ደግሞ ወዲያውኑ የሚበተን ነው። ይህ ከሆነ ቆይቷል። አሁን ያለው ብሔራዊ ቡድንም ለረጅም ወራት ተበትኖ ቆይቷል። ከዚህ በኋላ በዚ አይነት ሁኔታ አንቀጥልም። አሁን በዚህ አይነት ጊዜ የተገኘው ብሔራዊ ቡድን ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ አይደለም። የፈረሰው ነው እንደ አዲስ የተዋቀረው፤ ይህ የተዋቀረው ብሔራዊ ቡድን ረዘም ላለ ቀን ዝግጅት አድርጓል። ከዚ በኋላ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ሆኑ የቡድን ግንባታዎች የወደፊቱን ጠንካራ እና ተፎካካሪ ቡድንን በማሰብ ነው የሚከናወኑት። የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ከተሰባሰበ ጊዜ አንስቶ ያለው ነገር ጥሩ ነገር ነው። እዚህ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ እድል ያገኙ አዳዲስ ተጫዋቾች አሉ። ከሴራሊዮን ጋር በተደረገው ጨዋታ የታየው እንቅስቃሴም በጣም ከሚጠበቀው በላይ ነው።

” ጠንካራ ጎናችን አንድነታችን ነው። ተጫዋቾቹ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ውጤት ለማስመዝግብ ጥረት አድርገዋል። ለማሸነፍ የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው። በውስጣቸው የነበረው የማሸነፍ ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር በግልፅ የሚታይ ነበር። እንደ ቡድን የነበረውም እንቅስቃሴም ጥሩ ነበር።  ብሔራዊ ቡድኑ በርካታ ጎል አስቆጥሮ እንዲያሸንፍ ነበር ምኞታችን። ነገር ግን በጨዋታው የነበረው ችግር ይህ ነበር። በርካታ ጎል ማስቆጠር ሳንችል መቅረታችንን እንደ ድክመት እቆጥረዋለሁ። ይህን በሂደት ማስተካከል እንችላለን። በተለይ ወጣት አጥቂዎቻችን በዚህ ላይ ጠንክረው ከሰሩ በቀጣይ ይህን ችግር መቅረፍ ይቻላል፤ መቻልም አለብን።

ሁሌም የምንፈልገው አፍሪካ ዋንጫ የሚካፈልና በዓለም እግር ኳስ ተፎካካሪ መሆን የሚችል ብሔራዊ ቡድን መመስረት ነው። ነገር ግን ይህ ምኞት እውን እንዲሁን ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው። እኛም የምንፈልገው ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ስብዕና የተላበሰ እና ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን የሚችል ብሔራዊ ቡድን መፍጠር ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ለዚህ እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን።  “