ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአሰልጣኞቹን ክህሎት ለማሳደግ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና አዘጋጅቷል።
ከመፍረስ ስጋት ተላቆ በአዲስ የቦርድ አመራር ስር የተለያዩ ለውጦችን እያደረገ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቅርቡ ለሾማቸው አሰልጣኞቹ የሦስት ቀናት ስልጠና አዘጋጅቷል። ከ15 አመት በታች ቡድኑ እስከ ዋናዋቹ የወንድ እና የሴት ቡድኖቹ ድረስ በዋና እና በምክትል አሰልጣኝነት ቦታዎች ላይ በአመዛኙ ለቀድሞው ተጨዋቾቹ ኃላፊነት የሰጠው ክለቡ አሁን ደግሞ የተሿሚዎቹን አቅም ለማሳደግ ስልጠናውን አዘጋጅቷል።
የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኢሳያስ ደንድር ስለስልጠናው ያላቸውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሲገልፁ ” አሰልጣኞቻችን ያላቸው ክህሎት እንዳለ ሆኖ በተለያየ ጊዜ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እና ከወቅቱ እግር ኳስ ዕድገት ጋር አብረው ለመሄድ የሚያግዟቸው ስልጠናዎች እንደሚያስፈልጓቸው እናምናለን። ይህም የመጀመሪያው ይሆናል። በቀጣይም ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት በማድረግ ሌሎች ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት እናስባለን ” ብለዋል።
ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው ስልጠና ላይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የንድፈ ሀሳብ ስልጠናዎች የሚሰጡበት ሲሆን በመጨረሻው ቀን ደግሞ ጎፋ በሚገኘው የክለቡ ሜዳ ወይም በደንቦስኮ ሜዳ ላይ የመስክ ስልጠና ይሰጣል። በጥቅሉ በሁሉም ዕርከኖች በአሰልጣኝነት የሚሰሩ እና በምልመላ ላይ የሚገኙ 35 የክለቡ ባለሙያዎችም በስልጠናው ላይ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል። ስልጠናው ከ26 ዓመታት የሀገረ እንግሊዝ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመጣው አሰልጣኝ ሩፋኤል በረከት አማካይነት የሚሰጥ እንደሆነም ታውቋል። አሰልጣኙ በሚኖረው የሦስት ቀን ቆይታ አሰልጣኞቹ የሚገኙበትን ደረጃ መረዳት በዋናነት በዕቅድ አወጣጥ ፣ በተጨዋቾች እድገት እንዲሁም በሌሎች የአሰልጣኝነት ንዑስ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ ዕውቀቱን ለማካፈል እንደተዘጋጀ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጷል።
(በአሰልጣኝ ሩፋኤል በረከት የስራ ህይወት ዙሪያ ያደረግነውን ሰፊ ቃለ ምልልስ ነገ ለንባብ የምናበቃ ይሆናል)