ፌደራል ፖሊስ በሽረ እንደስላሴ ላይ ያስመዘገበው የተጨዋች ተገቢነት ክስ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ይግባኝ ብሏል።
ነሀሴ 14 በተደረገው የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ሽረ እንደስላሴ ፌደራል ፖሊስን 3-1 መርታቱ ይታወሳል። ሆኖም ፌደራል ፖሊስ በሽረ እንዳስላሴው ልደቱ ለማ ላይ የተጨዋች ተገቢነት ክስ አስይዞ የነበረ ቢሆንም የሊግ ኮሚቴው ክሱን ውድቅ በማድረግ የዕለቱ ውጤት እንዲፀና አድርጓል። ይህን ተከትሎ ፌደራል ፖሊስ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የይግባኝ ደብዳቤ አስገብቷል።
ክለቡ በደብዳቤው እንደገለፀው በተሻሻለው የዲስሊን መመሪያ መሰረት የሽረው ተጨዋች ልደቱ ለማ አምስት ቢጫ ካርድ ተመልክቶ አንድ ጨዋታ በቅጣት ያለፈው ቢሆንም የቅጣት ክፍያው ብር 1,500.00 የተከፈለው ጨዋታው ከጀመረ ከ30 ደቂቃዎች በኋላ መሆኑን ገቢ የተደረገበትን ደረሰኝ በማያያዝ አስረድቷል። በዚህም ምክንያት ክፍያው የተፈፀመው የቡድኖቹ አምበሎች በዳኞች ሪፖርት ማቅረቢያ ቅፅ ላይ ከፈረሙ በኋላ በመሆኑ ያቀረበው ክስ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባ እንደነበረ እና የሊግ ኮሚቴው ውሳኔ ሚዛናዊ አለመሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት ክለቡ ያቀረበው ማስረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁህ ጎል እንዲሰጠው እንዲሁም ያስያዘው አንድ ሺህ ብር ተመላሽ እንዲደረግለት ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አቤት ብሏል።
የፌዴራል ፖሊስ ማስረጃ እና ደብዳቤ ይህን ይመስላል:-