በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የውድረር ዓመቱን ያሳለፉት ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሰበታ ከተማ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን የአሰልጣኝ ቅጥር ፈፅመዋል።
ከአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ እንደማይቀጥል የተረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ የያሬድ ረዳት ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ዳዊት ሀብታሙን ወደ ዋና አሰልጣኝነት በማሳደግ የሁለት ዓመት የቅጥር ስምምነት ፈፅሟል። አሰልጣኝ ዳዊት በአዳማ ፕሮጀከት የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን ጀምረው በመቀጠል የአዳማ ከ17 ዓመት በታች እና የኦሮሚያ ምርጥ እንዲሁም የለገጣፎ ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መልካም አጀማመር አድርጎ የነበረው ሰበታ ከተማ ሥዩም ከበደን ወደ መከላከያ ከሸኘ በኋላ በምክትሉ ሲመራ ቆይቶ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ህልሙን ለማሳካት ክፍሌ ቦልተናን ምርጫው አድርጓል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ መድን እና ጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ የተጠናቀቀው የውድድር አጋማሽን በፌዴራል ፖሊስ አሰልጣኝነት ጀምረው በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ማምራታቸው የሚታወስ ነው።