ሩፋኤል በረከት ይባላል። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ሲሆን በ1985 መጨረሻ ላይ በ13 ዓመቱ ወደ እንግሊዝ ሀገር በመሄድ ኑሮውን በቋሚነት እዛው አድርጎ ቆይቷል። እንደሄደም ከትምህርቱ ጎን ለጎን ለትምህርት ቤቱ በመጫወት በእንግሊዝ ብሔራዊ የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ተሳትፏል። በመቀጠል በቻርልተን አትሌቲክ እና ሌይተን ኦርየንት ክለቦች አካዳሚ ውስጥ የመጫወት ዕድልን አግኝቷል። ” ከግራ መስመር በመነሳት በማደርገው እንቅስቃሴ በቴክኒክ ችሎታዬ እና በፍጥነቴ ቢሳቡም በወቅቱ በነበረው የእግር ኳስ አስተሳሰብ ምክንያት በተክለ ሰውነቴ እና በጉልበቴ ደስተኛ አለነበሩም ” የሚለው ሩፋኤል በትምህርቱ በመግፋት እና በአካውንቲግ በመመረቅ በሌላኛው የህይወቱ መስመር ቀጥሏል።
ሆኖም ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ከውስጡ አልወጣም። በ1998 ከመሰረተው ካታንጋ ከተባለው የሀበሾች ቡድን ጋርም በለንደን ስትሪት ሊግ ፣ ኢትዮጵያን በመወከል በቤካም አካዳሚ ውስጥ እንዲሁም በሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች በመዘዋወር የተለያዩ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እና የማሸነፍ አጋጣሚዎችም ነበሩት። በመቀጠል በፉትቦል ፋውንዴሽን ስር የተለያዩ ኮርሶችን በመውሰድ ወደ ስልጠናው ገብቷል። ህልሙ በነበረው የሕፃናት ስልጠና ላይም መስራት ጀምሯል። አሁን ላይ ከአንድ ባልደረባው ጋር በመሆን በዕድሜያቸው ከ5-12 የሆኑ በቁጥር ከ90 በላይ የሚሆኑ ሀበሾችን በመያዝ በሳምንት ሦስት ቀን በለንደን ሎፍተስ ሮድ የ ኪው.ፒ አር ስታድየም አቅራቢያ እያሰለጠነ ይገኛል። 2005 ላይ ለአጭር ጊዜ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የነበረው ሩፋኤል የሕፃናት ሊግ የመመስረት ሀሳብ የነበረው ቢሆንም እምብዛም ሳይገፋበት ተመልሷል። ነገር ግን በቅርቡ በድጋሚ ወደ መዲናችን የመጣው አሰልጣኙ ክረምቱን በጁቬንቱስ ክለብ በራሱ ተነሳሽነት ታዳጊዎችን ሲያሰለጥን ከርሟል። የሚመለስበትን ቀን በማራዘምም ከወጣት አሰልጣኞች ጋር በመገናኘት ያለውን ልምድ ሲለዋወጥ ቆይቶ ከትናንት ጀምሮ ደግሞ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኞች ለሦስት ቀናት የሚቆይ ስልጠናን በመስጠት ላይ ይገኛል። ወጣቱ አሰልጣኝ ትዳር መስርቶ የሁለት ልጆች አባት በሆነባት እንግሊዝ ከታዳጊነት ጊዜው አንስቶ ባሳለፈው የእግር ኳስ ህይወት እና በስልጠናው ዓለም ውስጥ ስላገኛቸው ቁምነገሮች እንዲሁም ስለቀጣይ ዕቅዶቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርጓል።
እንግሊዝ ሀገር በቆየህባቸው ጊዜያት በህፃናት እግር ኳስ ስልጠናው ምን ትምህርት አግኝተሀል ?
የኤፍ ኤውን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ኮርሶች ወስጃለው። ከዛ በላይም በህፃናት ስልጠና ላይ በስራ ውስጥ የምትማረው ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ ልጆችን በሚገባ ማወቅ ፣ እግር ኳስ ኳስን በመጫወታቸው ብቻ ሳይሆን በቤተሰባዊ እና ማህበራዊ መስተጋብራቸው ውስጥ የሚፈጠሩባቸውን ችግሮች ተረድቶ እና አቅርቦ በመረዳት መፍትሄ በመስጠት በሜዳ ላይ ትኩረታቸው እንዲሰበሰብ ማድረግን በልምድ የምታካብተው ነው። ከምንም ነገር በላይ ግን በሰዓት አጠባበቅ እና በዕቅድ አወጣጥ ላይ ሰፊ ትምህርት ወስጃለው። እናት እና አባቶች ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው አሰልጣኙ እስኪመጣ መጠበቅ የለባቸውም። እንደ አሰልጣኝም ሰፊ ዕቅድ ያስፈልጋል ፤ ልጆቹ ሲመጡ ይዘው ለሚመጧቸው ነገሮች የሚያሳዩትን ልዩነቶች ማዕከል ያደረገ ሰፊ ዝግጅትንም ይጠይቃል። ሁሉም በእግር ኳስ ህይወት ውስጥ ብቻ ስኬታማ እንዲሆኑም ስለማይጠበቅ በሌላው ህይወታቸው በስፖርቱ አማካይነት በስነምግባር ታንፀው እና ካላስፈላጊ ነገሮች ርቀው እንዲያድጉ ተፅዕኖ ማሳደርን ይጠይቃል።
የሕፃናት የእግር ኳስ ስልጠና ከአዋቂዎች አንፃር ስታየው ምን የተለየ ነገር አለው ?
ትላልቆች ላይ ኮስተር ማለት ትችላለህ። ለትናንሾቹ ላይ ግን አቀራረብህ ቀለል ያለ መሆን አለበት። በጣም ትዕግስተኛ መሆንንም ይጠይቃል። ያለትዕግስት መጀመርም ከባድ ነው። ትልልቆቹ ላይ የተጨዋቾችን ሁኔታ አይተህ በሌላ እስከመተካት ልትደርስ ትችላለህ። ህፃናት ላይ ግን ያን አታደርግም። ዕድሜያቸው ወርቃማ ነው። የተለያየ ዓይነት ተሰጥኦ ቢኖራቸውም በዕኩል ደረጃ መታየት አለባቸው። ስልጠናውም የሚያዝናናቸው ዓይነት መሆን አለበት። ደስተኛ ሆነው በኳሱ እየተዝናኑ እና እየተደሰቱ ሲሰለጥኑ ነው ተሰጧቸው ራሱን መግለፅ የሚጀምረው። ከዚህ አንፃር እንደውም የትላልቆቹ ቀለል ይላል።
አንተ በታዳጊነትህ ወቅት በእንግሊዝ የመጫወት ዕድል ነበረህ ፤ በአሰልጣኝነትም አውሮፓዊያኑን በቅርበት ተመልክተሀል። እዚህም መጥተህ ከታዳጊዎች ጋር ሰርተሀል። ከዚህ አንፃር ብዙ የሚያከራክረውን ጥያቄ መመለስ የምትችል ይመስለኛል። ባንተ እይታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ የእግር ኳስ ተሰጥኦ አለ ?
በትክክል ! እንግሊዝ ሀገር በጥሩ ሜዳ ላይ ሙሉ ትጥቅ ተሟልቶላቸው ነው የሚጫወቱት። እዚህ ደግሞ በተቃራኒው በብዙ ችግር ውስጥ ሆነው ኳስን ይጫወታሉ። ነገር ግን ከኳስ ጋር ሲገናኙ የሚያደርጉት ነገር በጣም አስገራሚ ነው። ሁኔታዎች ሳይመቻቹልህ መጫወት ከባድ ነገር ነው። ኳስ ይዘህ ራሱ አዕምሮህ ስለብዙ ነገር ማሰብ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ ኳስ እየገፋህ ተጋጣሚህን ለማለፍ ስትሞክር በዛው ቅፅበት ጫማህ እንዳይወልቅ ወይንም ሜዳው እንዳያሳስትህ ለማሰብ ትገደዳለህ። ይህ ቀላል አይደለም። እነዚህ ልጆች አውሮፓዊያኑ በሚሰጡት ስልጠናዎች ከህፃንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ቢገቡ እንደ ABC (Agility Balance and Coordination) ያሉ ስልጠናዎችን በቀላሉ ማለፍ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ። እዚህ አብሬያቸው በሰራሁባቸው 15 ቀናት ውስጥ እዛ ረጅም ጊዜ ይወስዱብኝ የነበሩ ስልጠናዎችን በቀላሉ ለመረዳት እንደቻሉ ተገንዝቢያለው። የስካንዴኔቭያን እና የእንግሊዝ ህፃናትን ተመልካቻቸዋለው። እኔም በዛ ዕድሜዬ አብሬያቸው ተጫውቻለው። በጊዜው እዚህ በላስቲክ ኳስ እና በቴዘር ስጫወት ቆይቼ እዛ ስሄድ በቴክኒኩ ብዙ እንዲገረሙብኝ ማድረግ ችዬ ነበር። ተደንቀው ሲጠይቁኝም ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ተጫውታችሁ ካላደጋችሁ ይህን ማድረግ አትችሉም’ እላቸው ነበር። አሁንም ያሉት ልጆች እንደዛ ናቸው። ፍጥነታቸው ፣ ኳስ አያያዛቸው አጠቃላይ ተሰጥኦዋቸው እጅግ የተለየ ነው። ፍላጎታቸው ደግሞ እጅግ የሚገርም ነው። ቁም ነገሩ በዕቅድ የተመራ ዕድገታቸውን የጠበቀ ስራ መስራት መቻሉ ላይ ነው እንጂ የትም መድረስ እንደሚችሉ አምናለው።
እኛ ሀገር ልምዱ ባይኖርም በአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ህፃናት እና ታዳጊዎች እንደ ዕድሜያቸው በተለያዩ ዕርከኖች ውስጥ አልፈው ዋናዎቹን ቡድኖች እስከማገልገል እና ትልቅ ተጨዋች እስከመሆን ይደርሳሉ። በስልጠናው ውስጥ ይህን እንዲያሳኩ የሚያስችላቸው ዋናው ነገር ምንድነው ?
በዋነኝነት አውሮፓ ውስጥ ተጨዋቾቻቸውን በጣም በቅርበት ነው የሚከታተሉት። በእያንዳንዶቹ ልጆች ዕድገት ላይ መሰረት የያደረገ ዕቅድ (Development Plan) አላቸው። ያላቸውን የቴክኒክ ዕድገት በአግባቡ ይመዘግባሉ። ከዓመት ዓመት የሚያሳዩትን ለውጥም ይመዝናሉ። ከዚህም ባለፈ በትዕግስት ጠብቀው እንዲሻሻሉ ዕድል ይሰጧቸዋል። በሥነምግባርም የታነፁ እንዲሆኑ ይጠብቃል። ችሎታ ብቻውንም በቂ አይደለም። ሥነ ምግባራቸውም አብሮ የተጠበቀ ካልሆነ እስከመቀነስ ይደርሳሉ። ዕረፍት እና አመጋገብም በልጆች ዕድገት ላይ ያላቸው ትልቅ ተፅዕኖ ሳይረሳ። ስለዚህ ዋናው ነገር ለእያንዳንዱ ልጅ የተናጠል የዕድገት ዕቅድ ማውጣት ፣ ለውጦቹን መመዘን እና ማስተካከያዎችን በማድረግ እንዲሻሻሉ በመርዳቱ ላይ ነው። ከዛ መከከል ደግሞ የተለየ ብቃት የሚያሳዩት ላይ ይበልጥ የቅርብ ክትትል በማድረግ እስከዋናዎቹ ቡድኖች ያመጧቸዋል። ክለቦች በዚህ ረጅም መንገድ ውስጥ ያለፉ የራሳቸውን ልጆች ማግኘት በሚኖራቸው የመለያ ፍቅር ምክንያት በግዢ ከሚመጡት ይልቅ በጣም ተጠቃሚ እንደሚያደርጓቸው ያምናሉ።
ክለቦቻችን በብዛት ከ 20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖች ነው ያሏቸው ፤ ከዛ በታች እምብዛም አይወሩዱም። አንተ እንደምታስበው ከ8 ዓመት ጀምሮ ልጆችን መያዝ ከ17 ወይም 15 ዓመት በታች ከመጀመር ጋር ሲነፃፀር ምን ያህል ለውጥ ይኖረዋል ?
በጣም ልዩነት አለው። በመጀመሪያ ደረጃ በስነምግባር። ከ8 ዓመታቸው ጀምረህ ስታገኛቸው በስፖርቱ ውስጥ እንዲያድጉ ከማድረግ ባለፈ የሚፈለገውን ስነምግባር እንዲይዙ ልታደርጋቸው ትችላለህ። ከአለባበስ ጀምሮ በሁሉም ነገር ዝግጁ የመሆን እና ስፖርቱ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ አምነውበት እና ተረድተውት ከመተግበር አንፃር የተለዩ ይሆናሉ። 15 እና 16 ላይ ሆነው ስታገኛቸው ጉርምስናውም ስላለ ለማቃናት ሊያስቸግር ይችላል። ከ8 ዓመት በፊት ግን ገና ከዛ ጊዜ ጀምሮ ከፍ ያሉትን በማየት እና እንደነሱ ለመሆን በሚያሳዩት ጉጉት ውስጥ የማደጉ ዕድል ይኖራቸዋል። አካላዊ በሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ስትመለከተው ከ8 አመት በታች በመጀመር በአመጋገብ ብዙ ልዩነትን ማምጣት ይቻላል። በስልጠናው ፣ በጨዋታዎች እና በውድድሮች ውስጥ ከሚያካብቱት ልምድ ባለፈ ለእግር ኳስ ብቁ የሆነ የአካል ብቃትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ከ15 እና ከ 16 ስትጀምር የምታጣው ሌላው ነገር መሰረታዊ የሆኑትን ብቃቶች ነው። በርግጥ ኳሱን ይችሉታል እኮ ግን ከታች የተሰራባቸውን ስትመለከታቸው ደግሞ ይበልጥ ሜዳ ላይ ተረጋግተው ከኳስ ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የመተግበር እና ተረጋግተው የሚፈልጉትን ውሳኔ የመወሰን ብቃት ትመለከትባቸዋለህ። ለምሳሌ ኳስ ሲቀበሉ ዙሪያቸውን ማየት እና ሰፋ ባለ ዕይታም ተረጋግየው የማቀበል ችሎታ ይኖራቸዋል። ለአብነትም እንግሊዝ ውስጥ እነ አርሰናል እና እነ ቶተንሀም ሌሎቹም ቡድኖች የ8 ዓመት በታች ቡድኖች አሏቸው። ዕሁድ ቀን ጨዋታዎች ያደርጋሉ። በሌሎቹም የዕድሜ እርከኖች እንደዛው። ይህ በመሆኑም እግር ኳስ በሚፈልጋቸው ሁሉም መስፈርቶች እየተሻሻሉ ትልቅ ለመሆን ነገሮች ቀላል ያደርግላቸዋል።
በሀገራችን በአሰልጣኝነት ሙያ በቅርብ ዓመታት ስኬታማ ወጣቶችን በብዛት እያየን አንገኝም። በቶሎ ወደ ላይኛው የእግርኳሱ ዕርከን ላይ ለመድረስ የመፈለግ ችግርም ይስተዋላል። በሕፃናት ስልጠና ላይ ትኩረት ከመስጠት አንፃር ወጣት አሰልጣኞች ምን ይጠቀማሉ ?
መራመድ ከመጀመር በፊት በዳዴ መሄድ የግድ ይላል። ከመሰረታዊው ነገር መጀመር አስፈላጊ ነው። ትዕግስት ደግሞ ዋነኛው መሳሪያ ነው። ትጋት ያስፈልጋል። አሰልጣኝነት ትላልቅ ክለቦችን በማሰልጠን ወይም ውጤት በማምጣት ብቻ የሚገለፅ አይደለም። ተጨዋቾችን ከህፃንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ መስራት መቻል በራሱ ትልቅ ስኬት ነው። አሰልጣኞች ስለራሳቸው ብቻ ማሰብ የለባቸውም። ስለሚያሳድጓቸው ተጨዋቾች መጨነቅ ይገባቸዋል። ለራሳቸውም ስኬታቸውን ከዛ አንፃር መለካት ይኖርባቸዋል። ለውያው እና ለራሳቸው ታማኝ ሆነው መስራት ከቻሉ ትልቅ ደረጃ መድረሳቸው አይቀርም። ነገር ግን ሁሉም ነገር ከስር የሚነሳ መሆኑን ማመን ይኖርባቸዋል።
ከስድስት ዓመት በፊት መጥተህ ነበር በወቅቱ ምን ለመስራት አስበህ ነበር ?
እንግሊዝ ውስጥ እግር ኳስ በጣም ትልቅ ቁም ነገር ፤ ህይወትም ነው። የታዳጊዎችን ብዙ ነገራቸውን የማስተካከል ኃይል አለው። ያኔ ስመጣ ይሄን አስቤ ነበር የመጣሁት። አካዳሚ በመክፈት ልጆችን በመያዝ እንዲሁም የሂሳብ እና የእንግሊዘኛ ትምህርቶችም ጎን ለጎን በማገዝ ለመፅሀፍትም ቅርብ እንዲሆኑ በማስቻል ጥሩ ሆነው ወጥተው በኳሱ ብቻ ሳይሆን በሌላው ህይወታቸውም ከፍ ያለ ቦታ ላይ እንዲደርሱ አስብ ነበር። በአንድ አጋጣሚ ብሔራዊ አካባቢ ጎዳና ላይ ከወደቁ ልጆች መካከል አንዱ መሬት ያለን የውሃ የፕላስቲክ ዕቃን በሚያስገርም ቴክኒክ ሲያነሳ ተመልክቼ ለሁለት ሳምንት ፈልጌው ሁላ አጣሁት። በሌላ ጊዜ ደግሞ ማዘጋጃ አካባቢ ሌላ ታዳጊ ጎማ በሽቦ እየነዳ በዛው ቅፅበት ኳስን ሲገፋ አይቼ በጣም ተደንቄ ነበር። እነዚህ ልጆች ዕድሉን አግኝተው ቢሰራባቸው እና በእግር ኳስ ውስጥ ቢያልፉ በትምህርትም ቢታነፁ ከገቡበት ህይወት መውጣት እና ወደተሻለ መንገድ መግባት እንደሚችሉ አምናለው። ነገር ግን በወቅቱ ይህን ለማድረግ ስመጣ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውኝ ነበር። ቤተሰባዊ ኃላፊነቶችም ስለነበሩብኝ ሀሳቤን ሳላሳካ ነበር የተመለስኩት።
አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተሀል። ከመጀመሪያው በተለየ መልኩም በቆይታህ ጥሩ ልምድ እያገኘህበት ነው። ከታዳጊዎች ጋር የመስራት እና ከአሰልጣኞች ጋር የመገናኘት ዕድሎችን ፈጥረሀል። በቀጣይስ ምን ታስባለህ ?
እኔ ለምሳሌ ከሃገር ሳልወጣ በፊት ህፃን እያለው ጁቬንቱስ ክለብ ተጫውቻለው። የሚገርም ፉክክር ነበር። አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ቆሟል። ምንም ውድድር አለማየቴ በጣም አስገርሞኛል። የልጆችን ክህሎት ለማየት ውድድር ሲኖር የበለጠ ጠቃሚ ነው። ማሸነፍ እና መሸነፉን ማለቴ ሳይሆን ያላቸውን ነገር አውጥተው የሚያሳዩበት መድረክ ከመፍጠር አንፃር ማለቴ ነው። እና ብሔራዊ የልጆች ሊግ ስለመመስረት አስባለው። ከ8 እስከ 10 ከ11 እስከ 13 ባሉት የዕድሜ ክልሎች ውስጥ ትምህርት ቤቶች ቡድኖች ኖሯቸው በሳምንት አንድ ቀን በውድድር ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ከነዛ መሀል የተመረጡ ልጆችን ማግኘት ይቻላል። እነዛን ልጆች በዳና ካፕ እና ጎቲያ ካፕ የመሳሰሉ አውሮፓ ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ መውሰድ ይቻላል። በዛ አጋጣሚም በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ዓይኖች ውስጥ የመግባት ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በነዚህ ውድድሮች ላይ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች የመሳተፍ ዕድል አግኝተዋል፤ ለኛም ልጆች ያንን ማድረግ ይኖርብናል። ልጆቹ ዕድሉን ሲያገኙ እና ሀሳቡም ሲሰፋ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም የመሳተፍ ፍላጎት እንደሚያሳድሩ አስባለው። ለዚህ ደግሞ ዕድሜያቸውንም በሚገባ ለመቆጣጠር በክለቦች ሳይሆን በትምህርት ቤቶች ሊግ መጀመር እንዳለበት አምናለሁ።
በዚህ ረገድ እስካሁን ምን ምን ተግባሮችን አከናውነሀል ? ምክንያቱም አዲስ ነገር ለመጀመር ሲታሰብ ፈተናው ብዙ ይሆናል እና ጥሩ ተስፋ አይተህበታል ?
ለወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስተር ምክረ ሀሳቤን አስገብቻለው። ጉዳዩ በቀጥታ እንደሚመለከተውም አስባለው ወጣቶችን ከማብቃት አንፃር። በቀጣይ ትምህርት ቤቶችን የማናገር ሀሳብ አለኝ። በዚህ መልኩ የማይሳካ ከሆነ ግን ልጆቹን በቀጥታ የመመልመል ሃሳብም አለኝ፤ እንደ ሁለተኛ ዕቅድ ማለት ነው። እኔ በግሌ አንድ ነገር ስጀምር ይሆናል ብዬ ነው የምጀምረው። በብዛትም ይሳካልኛል። ብዙ እንደሚረዱኝ ማስባቸው ሰዎችም አሉ። እኔ ገንዘብ አይደለም የምፈልገው። ወይም ቁሳቁሶችንም አይደለም። ሁሉም ነገር አለኝ። በስፖንሰርሺፕነትም እንደሚረዱኝ ቃል የገቡልኝም አካሎች አሉ። ዋናው አላማዬ ልጆቹን ትልቅ ቦታ ላይ ማድረስ ነው።
ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ አሰልጣኞች ጋር ለማድረግ ስላሰብከው ቆይታም ጥቂት በለኝ (ስልጠናውን ከትናንት ጀምሮ እየሰጠ ይገኛል)
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ1953 የተመሰረተ ትልቅ ክለብ ነው። ትናንትና የመጣ አይደለም ፤ ምንም እንኳን ቢወርድም አሁን ጥሩ መነቃቃት ላይ ናቸው። ወደ ነበሩበት ደረጃ የመመለስ እምነቱም እንዳላቸው ተመልክቻለው። ደጋፊዎቹም በነሱ እና በተጨዋቾቹ ላይ ከፍተኛ ዕምነት አላቸው ፤ አይዟችሁ በርቱ ማለታቸው ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ይሄ ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል። ስለዚህ እኔም እንግሊዝ ሀገር በቆየውባቸው ጊዜያት የተማርኳቸውን ነገሮች ወደነሱ ባስተላልፍ እነሱ ደግሞ ተጨዋቾቻቸው ላይ ቢተገብሩት ጥሩ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አስባለው። እኔም ከነሱ የምማረው ብዙ ነገር ይኖራል። በዕቅዴ መሰረት የሦስት ቀናት ቆይታ ይኖረናል። ሁለቱን ቀን በክፍል ውስጥ መጨረሻ ላይ ደግሞ በሜዳ ላይ። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም የአሰልጣኞቹን ደረጃ እና ያላቸውንም አቅም መረዳት ይጠበቅብኛል። ቅድም ያልኩህ የዕድገት ዕቅድ (Development Plan) ላይ ትኩረት ለማድረግ አስቤያለው። ለአንድ የቡድን ዲፓርትመንት ብቻ የሚዘጋጁ ስልጠናዎች ላይም የማተኮር ሀሳብ አለኝ። እነዚህን እና ሌሎችን በከፍተኛው ስልጠና መድረክ ላይ ሲተገበሩ ያየኋቸውን ነገሮች በሙሉ ማካፈል አስቤያለው።
በቅርቡ ተመልሰህ መሄድህ አይቀርም። በቀጣይ ተመልሰህ መጥተህ ስለመስራት ምን ታስባለህ ?
እውነት ለመናገር ቶሎ እመለሳለው። ሀገሬ እዚህ ነው ፤ ተወልጄ ያደኩት ማለፍም የምፈልገው እዚሁ ነው። 26 ዓመት ጠብቄያለሁ። ያሰብኳቸው ነገሮች ከተሳኩ እዚህ መቆየት ካለብኝ ሙሉ ለሙሉ መምጣትም ካለብኝ አደርገዋለው ባለቤቴም ብዙ ትደግፈኛለች። ዋናው ነገር ልጆቹ ላይ ለስራ ያሰብኳቸው ነገሮች መሳካታቸው ላይ ነው። ሁሉም ነገር ግን በዕቅድ የሚመራ ነው። እንግሊዝ ሀገር የማውቃቸውን ሰፊ ልምድ ያላቸው ከኔ የበለጡ አሰልጣኞችንም ወደዚህ መጥተው ትምህርት እንዲሰጡ ስለማድረግም አስባለው።
እዚህ ሀገር ላሉ ባለሙያዎች አብረውህ እንዲሰሩ ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ ?
ከዚህ ሀገር ከወጣው ቆይቻለው። እግር ኳስ ውስጥ እየሰሩ ያሉ ውጪ ያሉትም መጥተው እዚህ ያሉትም ተባብረው ሀገራችን ውስጥ ያለውን ክህሎት ማውጣት እንደምንችል አስባለው። ሁላችንም ተባብረን መስራት ከቻልን እንደ ፓናማ ነገ በዓለም ዋንጫ የሚወክሉንን ልጆች ካሁን ማፍራት እንችላለን። ይህ ደግሞ የግድ ነው። ሆኖ ማየት አለብን። ይህን ማድረግ ካልቻልን ትልቅ ውድቀት ነው።