ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ – የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ

ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2008

09፡00 – አዲስ አበባ ስታድየም

 


 

ለሁለቱ ታሪካዊ ቡድኖች 2008 ታሪካቸውን የሚዘክሩበት አመት ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተመሰረተበትን 80ኛ አመት መከላከያ ደግሞ 70ኛ አመት የሚያከብሩት በዚህ አመት ጥር ወር ላይ ነው፡፡ አመቱን በድል ሟሽተው በአላቸውን ለማድመቅ ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ፍፃሜውን መቀላቀል ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

ወቅታዊ ሁኔታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሆላንዳዊው ማርቲን ኩፕማን እየተመራ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ ሲያደርግ የሰነበተ ሲሆን በዚህ አመት ለሚካሄዱ ውድድሮች በከፍተኛ ትኩረት እየተዘጋጁ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ ለ1 ወር ያህል በአዳማ የቆየ ሲሆን ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል፡፡ በቅርቡም በከተማው ከሚገኘው የኦሮሚያ ሊግ ክለብ ሪፍት ቫሊ ጋር ባደረገው ጨዋታ 4-0 አሸንፏል፡፡ በሙከራ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች እና አዲሶቹ ፈራሚዎች ራምኬልና አስቻለውን ጨምሮ በብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ከቡድኑ የተለዩት ተጫዋቾች ተመልሰው ቡድኑ የተሟላ ስብስብ ይዟል፡፡

አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን ከክለቡ ልሳን ጋር ባደረጉት ቆይታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለጨዋታው ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በቅድሚያ ስንሰራ የነበረው ለሁሉም ጨዋዎች ብቁ የሚደርገንን የአካል ብቃት እና የታክቲክ ስራዎች ነበር፡፡ የጨዋታውን ቀን ካወቅን በኋላ ግን ተጫዋቾቼ በአካልም ሆነ በአእምሮ ዝግጅት እንዲያደርጉ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ረዳት አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታም በተመሳሳይ ለጨዋታው ትኩረት መስጠታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፃዋል፡፡ ‹‹ ክለባችን ሁሌም ትኩረት የሚያደርገው ከፊታችን የሚጠብቀንን ፍልሚያ በድል መወጣት ላይ ነው፡፡ ለጨዋታው ከፍተኛ ዝግጅት ያደረግን ሲሆን አዲስ የፈረሙትም ሆነ ከወጣት ቡድን ያደጉት ተጫዋቾች የሚያሳዩት ትጋት አስደሳች ነው፡፡ ›› ሲሉ ለጨዋታው ትኩረት እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡

የገብረመድህን ኃይሌው መከላከያ በአዲሱ አመት አንዳንድ ለውጦች አድርጎ መጥቷል፡፡ በተለይም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት የተጠቀሙበትን የተከላካይ መስመር በአዳዲስ ተጫዋቾች ተክተዋል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ እና ካርሎስ ዳምጠው ደግሞ የአጥቂ ክፍሉ ላይ ፍጥነት እና ጉልበት ይጨምራሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡

አሰልጣኝ ገብረ መድህን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደማስፈረሙ ቡድኑን ለማዋሃድ ሳምንታት እንደሚፈጁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ አዳዲስ ፈራሚዎቸ እና ከወጣት ቡድን ያደጉ ተጫዋችን አዋህዶ ወደ አንድ ለማምጣት ቢያንስ 7 ሳምንት ያስፈልገናል፡፡ ዝግጅት የጀመርነውም ቀደም ብለን ነው፡፡ ቡድኔን ለማዋሃድ ስራዎች በምንሰራበት ሰአት መስከረም 11 ጨዋታ እንዳለን ከፌዴሬሽኑ የተነገረን በነሃሴ መጨረሻ ነው፡፡ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ ባለብን ሰአት የፕሮግራም አወጣጡ ተፅእኖ ፈጥሮብናል፡፡ ነገር ግን ይህንን እንደምክንያት ማቅረብ አንፈልግም፡፡ በ2016 የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ መሳተፍ ስለምንፍልግ ለጨዋታው ከፍ ያለ ትኩረት እና ግምት ሰጥተናል፡፡ ያለንን ሁሉ አውጥተን በመጫወት የምንፈልገውን ውጤት በእጃችን እናስገባለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ጦሩ በቢሾፍቱ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በቅርቡ አዲስ አበባ ዝግጅት በማድረግ ላይ ካለው ሶማሊያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጎ 0-0 ተለያይቷል፡፡

 

ጉዳት እና ቅጣት

ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በቅጣት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች የለም፡፡ አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ በልምምድ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለጨዋታው የማይደርስ ሲሆን ለሙከራ ፖርቱጋል የሚገኙት ሳላዲን በርጌቾ እና ናትናኤል ዘለቀም ይህ ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡ በእጁ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው በኃይሉ አሰፋ ከጉዳቱ ቢያገግምም በጨዋታው የመሰለፍ እድሉ አጠራጣሪ ነው፡፡

ከመከላከያ በኩል በቅጣት የማይሰለፍ ተጫዋች ባይኖርም አዲሱ ፈራሚ ሚልዮን በየነ እና አምበሉ ሚካኤል ደስታ በጉዳት አይሰለፉም፡፡

 

ቁልፍ ፍጥጫዎች

ባዬ ገዛኸኝ ከ አስቻለው ታመነ

ሁለቱ ወጣቶች ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፡፡ ሁለቱም የየክለቦቻቸው አዲስ ፈራሚዎች ናቸው፡፡ ለብሄራዊ ቡድን በቋሚነት የሚጠሩ ሲሆን አስቻለው ቋሚ ተከላካይ ፣ ባዬ ደግሞ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ ነው፡፡ ባዬ በመከላከያ አስቻለው በጊዮርጊስ የሚከፈላቸው ደሞዝ በሃገሪቱ ከፍተኛ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፉ ናቸው፡፡

ባዬ አምና የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር ከፈተኑ ጥቂት ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡ ፍጥነቱ ፣ ጉልበቱ እና ጫና የመፍጠር ችሎታው ተከላካዮችን እረፍት ይነሳል፡፡ አስቻለው በበኩሉ በዚህ ሰአት የሊጉ ምርጥ ተከላካይ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን እና ደደቢት ያሳየውን በቅዱስ ገዮርጊስም እንደሚደግመው ይጠበቃል፡፡

ብሪያን ኡሞኒ ከ አዲሱ ተስፋዬ

ዩጋንዳዊው አጥቂ ቀስ በቀስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተላምዷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በጊዮርጊስ የመጀመርያ ሙሉ የውድድር አመቱን ይጀምራል፡፡ አምና ወሳኝ ግቦች ካስቆጠረው ብሪያን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ብዙ ይጠብቃሉ፡፡ በማክሰኞው ጨዋታ ብሪያንን ሊፈትን ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው በክረምቱ ከወላይታ ድቻ የመጣው አዲሱ ተስፋዬ ነው፡፡ ጠንካራው ተከላካይ የአየር ላይ ኳሶችን የመከላከል ብቃቱ እና ጉልበቱ ለብሪያን ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዘካርያስ ቱጂ ከ ማራኪ ወርቁ

ዘካርያስ የአምናው ክስተት ነበር፡፡ ፉክክር የነበረበትን ቦታ ወጥ አቋም በማሳየት በቋሚነት ከመያዙ ባሻገር የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን እስከማድረግ ደርሷል፡፡ ማራኪ ደግሞ ከጉዳት መልስ በውድድር አመቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች አስገራሚ አቋም አሳይቷል፡፡ ግቦች ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ፍጥነቱ ለመስመር ተከላካዮች ራስ ምታት ነው፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች በማክሰኞው ጨዋታ በአንድ መስመር ላይ ከተገናኙ የጨዋታውን ውጤት ሊወስን የሚችል ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡

 

እንዴት መጡ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ግማሽ ፍፃሜው የተጫወተው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ በሰኔ ወር አጋማሽ አርባምንጭ ከነማን በናትናኤል ዘለቀ ግሩም ግብ ታግዞ 1-0 በማሸነፍ ለማክሰኞው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በቅቷል፡፡

መከላከያ በጥር ወር አጋማሽ ዳሽን ቢራን 2-0 አሸንፎ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ሲሆን በሩብ ፍፃሜው ሲዳማ ቡናን በምንይሉ ወንድሙ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና ፍሬው ሰለሞን ግቦች 3-0 በማሸነፍ ለማክሰኞው ፍልሚያ ደርሷል፡፡

እውነታዎች

ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን ጨዋታ በድል ከተወጣ ለ6ኛ ተከታታይ ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚ ይሆናል፡፡ (በ2004 ውድድሩ አልተካሄደም) ጊዮርጊስ በ2000 በሀዋሳ ከነማ ተሸንፎ ለፍፃሜ መድረስ ሳይችል ከቀረ በኋላ ባሉት 5 ውድድሮች በሙሉ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ በ2001 እና 2003 ዋንጫውን ሲያነሳ በ2002 እና 2006 በደደቢት በ2005 ደግሞ በመከላከያ ተሸንፏል፡፡

መከላከያ ይህንን ጨዋታ ካሸነፈ በ3 አመት ውስጥ ሁለተኛ የፍፃሜ ጨዋታውን ያሳካል፡፡ ከ2005 በይደር ወደ 2006 የተሸጋገረውን የፍፃሜ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምቶች አሸንፎ ባለ ድል ሆኗል፡፡

ይህንን ዋንጫ በርካታ ጊዜ በማንሳት ሁለቱን ክለቦች የሚስተካከል የለም፡፡ መከላከያ (በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጦር ኃይሎች በደርግ ዘመን ደግሞ ምድር ጦር የሚል ስያሜ ነበረው) ለ12 ጊዜያት ያህል በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ ቅዱስ ጊዮርጊስ (በደርግ ዘመን አዲስ ቢራ) 10 ጊዜ በማሸነፍ ይከተላል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና (ንጋት ኮከብ እና ቡና ገበያ) 5 ጊዜ ኤሌክትሪክ (መብራት ኃይል) ደግሞ 4 ጊዜ ይህንን ውድድር አሸንፈዋል፡፡

 

ያለፉት 4 የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ውጤት

ቅዱስ ጊዮርጊስ – አሸነፈ – አቻ (በመለያ ምት አሸነፈ) – ተሸነፈ – አሸነፈ

መከላከያ – አሸነፈ – ተሸነፈ – አሸነፈ – አሸነፈ

 


 

ምንጭ ካልጠቀስን በቀር በድረ-ገፁ ላይ የሚወጡ ፅሁፎች በሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፉን ለህትመት ፣ ለኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎች እና ለድረ-ገፆች ሲጠቀሙ ምንጭ በመጥቀስ ለስራችን ዋጋ ይስጡ

እናመሰግናለን !

ያጋሩ