ሰኞ መስከረም 07 2011
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ያደረገው ውይይት የገለልተኛ ሜዳ ጨዋታዎችን ለማስቀረት ከስምምነት በመድረስ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራር በዚህ ዓመት በየስታድየሞቹ ሠላማዊ እግር ኳስ እንዲታይ በማሰብ ከለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልል ክለቦች መካከል በገለልተኛ ሜዳ ሲደረጉ የነበሩ ጨዋታዎችን ለማስቀረትም ከዚህ ቀደም በካፒታል ሆቴል በርካታ የመንግስት አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ስብሰባ አድርጎ ሁለቱ ክልሎች የቤት ስራቸውን ይዘው እንዲሄዱ አድርጎ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ የዚህ ጥረት አካል የሆነ ስብሰባ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እንዲሁም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ኮሎኔል አወል በተገኙበት ተደርጓል። ስብሰባው ሲጀመር በ2010 የውድድር ዓመት በትግራይ ክልል መቀመጫቸውን ያደረጉ ክለቦች ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች እንዲሁም የደረሱበት ደረጃ የተነገረ ሲሆን በመቀጠል በስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ላይ የተደረገ ጥናት ለተሳታፊዎች ቀርቧል።
በመቀጠል ተሳታፊዎቹ ወደ ውይይት አምርተዋል። ከውይይቱ በኋላም የትግራይ እና የአማራ ክልል ክለቦች ቀድሞ ወደ ነበረው መልካም ግንኙነታቸው ተመልሰው ስፖርታዊ መርሆችን ባማከለ ሁኔታ መወዳደር እንደሚገባቸው ታምኖበታል። በመሆኑም በዘንድሮው የውድድር ዓመት በከፍተኛ እና አንደኛ ሊጎች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ጨምሮ በትግራይ ክልል በፕሪምየር ኒጉ የሚወዳደሩ አራት ክለቦች ከአማራ ክልል ከሚመጡ ክለቦች ጋር የሚደረጉ ጨዋታዎችን ያለምንም የፀጥታ ችግር በሜዳቸው ለማስተናገድ ተስማምተዋል። ተጋጣሚ ክለቦችን በሰላም ተቀብለው በሰላም ለመሸኘትም ቃል የገቡት ተሳታፊዎቹ በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ተነሳሽነት የሚኖር ከሆነ ከሜዳ ውጪ ያሉትን ጨዋታዎችም ለማድረግ ፍቃደኝነታቸውን ገልፀዋል። ይህንንም ለማድረግ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ተመሳሳይ መድረክ ከአማራ ክለቦች ጋር እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በተጨማሪም በ2010 የውድድር ዓመት በመቐለ እና ወልዋሎ መካከል የተከሰተው ስፖርታዊ ጨዋነት ችግርም የውይይቱ አካል የነበረ ሲሆን በሁለቱም ክለቦች ዙሪያ የተከሰቱት ጉድለቶች በግልፅ ለውይይት ቀርበው በስተመጨረሻም ዳግም እንዲህ አይነቱ ችግር እንዳይከሰት ቃል በመገባባት ስብስባው ተጠናቋል።