ረቡዕ መስከረም 09 2011
ወደ አንደኛው ዲቪዚዮን ከፍ ያለው አርባምንጭ አራት አዳዲስ ተጨዋቾችን አስፈርሟል። ሁለት ተጫዋቾችን በማሳደግ የነባሮችንም ውልም አድሷል።
በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ጥረት ኮርፖሬትን በመከተል በሁለተኝነት አጠናቆ ወደ መጀመሪያው ዲቪዚዮን ማደግ የቻለው አርባምንጭ አዳዲስ ተጨዋቾችን እያስፈረመ ይገኛል። በዚህም መሰረት የአራት ተጨዋቾችን ለሁለት ዓመታት በሚቆይ የኮንትራት ጊዜ በእጁ ያስገባ ሲሆን ተከላካይ መስመር ላይ ዝናቧ ሽፈራውን ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ትዕግስት አዳነን ከጌዲዮ ዲላ ማስፈረም ችሏል። አማካይ ክፍሉን ለማጠናከር ደግሞ ትሁት አየለን ከሀዋሳ ከተማ ያስመጣው አርባምንጭ የሲዳማ ቡናዋን የመስመር አጥቂ ቱሪስት ለማንም ከቡድኑ ጋር ቀላቅሏል።
አርባምንጭ ከተማ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ከማምጣት ባለፈም ረድኤት ዳንኤል እና ወርቄ ላቶን ወደ ዋናው ቡድኑ አሳድጓል። ክለቡ በዋናው ቡድኑ ሲያገለግሉ ከቆዩት ተጨዋቾቹ መካከል ደግሞ አዚዛ ታዬ ፣ ተስፋነሽ ተገኔ ፣ መሰረ ማቲዮስ ፣ የትምወርቅ አሸናፊ እና አበባዬ ጣሰውን ለቀጣይ ሁለት ዓመታት እንዲቆዩ ውላቸውን እንዳራዘመ ተሰምቷል።