ረቡዕ መስከረም 09 ቀን 2010
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ደቡብ ፖሊስ ዘግይቶ በገባበት የዝውውር መስኮት በስፋት እየተሳተፈ ይገኛል።
የከፍተኛው ሊግ ቻምፒዮኑ ደቡብ ፖሊስ ከስምንት ዓመታት በኋላ ለተመለሰበት የፕሪምየር ሊግ ፉክክር ለመዘጋጀት በአዳዲስ ተጨዋቾች ራሱን እያጠናከረ ነው። ከዚህ ቀደም አምስት ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ የቀላቀለው ክለቡ አሁን ደግሞ ሦስት የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾችን ማስፈረሙ ተሰምቷል።
የድሬዳዋ ከተማው ዘላለም ኢሳያስ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን በዝውውሩም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞው ክለቡ ተመልሷል። ሌላኛው ፈራሚ ደግሞ አዲስአለም ደበበ ነው። በሲዳማ ቡና ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ያለፉትን አመታት ሲጫወት የቆየው አዲስአለም አሁን ደግሞ ወደ ሌላኛው የደቡብ ክለብ አምርቷል። በሲዳማ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ እና ኢኮስኮ በመጫወት ያሳለፈው ሌላኛው አማካይ አሳምነው አንጀሎም ወደ ፖሊስ ያመራ ተጨዋች ሆኗል።
ሦስቱም ተጨዋቾች ነገ በይፋ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት እንደሚረከቡ ከሚጠበቁት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር በሲዳማ ቡና አብረው መስራታቸው የሚታወስ ነው። በተለይም አሳምነው ድሬደዋንም ጨምሮ ከአሰልጣኙ ጋር ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚገናኝ ይጠበቃል።