የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ማረፊያ ሀዲያ ሆሳዕና ሆኗል

በደቡብ ፖሊስ እና ሀድያ ሆሳዕና መካከል የውዝግብ ምንጭ የነበረው የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጉዳይ ዕልባት አግኝቷል።

ከቀናት በፊት በድረ ገፃችን እንዳስነበብነው ደቡብ ፖሊስን ወደ ሊጉ ያሳደጉት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከክለቡ ጋር የመቆየታቸው ወይንም ወደ ሀድያ ሆሳዕና የማምራታቸው ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል። ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኙ ከኔ ጋር ውል እንዳለው ነው የማውቀው ሲል አሰልጣኙ ደግሞ በወላጅ እናታቸው ህመም እና በሌሎች ምክንያቶች ከአዲሱ የፕሪምየር ሊግ አዳጊ ክለብ ጋር እንደማይቀጥሉ ማስታወቃቸውን ብሎም ለማንኛውም ክለብ አለመፈራረማቸውን ገልፀው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላው የደቡብ ክለብ ሀድያ ሆሳዕና ከአሰልጣኙ ጋር መስማማቱን እና መፈራረሙንም ጭምር አረጋግጦ ነበር።

ከአምስት ቀናት ቆይታ በኋላ ግን ዛሬ የአሰልጣኙ የመጨረሻ ማረፊያ ሀዲያ ሆሳዕና መሆኑ ተረጋግጧል። ክለቡ ከቀድሞው አሰልጣኙ ክፍሌ ቦልተና ጋር የመለያየቱን የሚገልፀውን ደብዳቤ በማቅረቡ እና ደቡብ ፖሊስ ከአሰልጣኙ ጋር ይፋዊ የውል ስምምነት እንደሌላቸው በመረጋገጡ ነው ሆሳዕና አዲሱን አሰልጣኝ በእጁ ያስገባው። በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሆሳዕናን ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ህልምን የማሳካት ኃላፊነት ይዘው ቀጣዩን የውድድር ዓመት ይጀምራሉ።

አሰልጣኝ ግርማ ከዚህ ቀደም ሀዲያ ሆሳዕናን ለረጅም ጊዜያት ያሰለጠኑ ሲሆን በ2007 ድሬዳዋ ላይ በተካሄደደው የብሔራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ክለቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ መርዳታቸው የሚታወስ ነው።