ደቡብ ፖሊስ ዘላለም ሽፈራውን አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ ከዋና አሰልጣኙ ግርማ ታደሰ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ከዘላለም ሽፈራው ጋር ለመስራት መስማማቱን ክለቡ አስታውቋል። 

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከድሬዳዋ ከተማ ከተለያዩ በኋላ ለጥቂት ወራት ያለ ስራ ቆይተው ከግንቦት ወር ጀምሮ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ወልዲያን መርተዋል። ደቡብ ፖሊስ ከግርማ ታደሰ ጋር የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ መልክ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አሰልጣኝ ዘላለም ቡድኑን ለመረከብ እንደተስማሙ ሲነገር የቆየ ሲሆን በመጨረሸመም የቀድሞ ክለባቸው ደቡብ ፖሊስን በአንድ ዓመት ውል ለማሰልጠን ከስምምነት መድረሳቸውን የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል አረጋግጠዋል።

ደቡብ ፖሊስ በ2000 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ተሳትፎውን እንዲያደርግ የረዱት አሰልጣኝ ዘላለም በ2002 ከቡድኑ ጋር ከተለያዩ በኋላ በደደቢት፣ አዳማ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልዲያ እና በብሔራዊ ቡድን ሰርተዋል።