ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን መቀነሱን ቀጥሏል

በሀዋሳ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በማድረግ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ተጨማሪ 3 ተጫዋቾችን ከቡድኑ ቀንሷል፡፡ አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች በአቋማቸው ደስተኛ ያልሆኑባቸው ዮናስ ገረመው ፣ ሐብታሙ ረጋሳ እና ሚካኤል በየነን ከቡድኑ ለመቀነስ ወስነዋል፡፡

የሶስቱ አማካዮች መቀነስ በቅድመ ውድድር ዝግጅቱ ከቡድኑ የተቀነሱት ተጫዋቾችን ቁጥር 6 ያደረሰው ሲሆን ከዚህ በፊት አቢኮዬ ሻኪሩ ፣ ጌቱ ተስፋዬ እና ደረጄ ኃይሉ መቀነሳቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና 6 ተጫዋቾችን ቢቀንስም ሌሎች 6 አዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን ተቀላቅለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና በደረሰን መረጃ መሰረት 3 ተከላካዮች ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ፣ ግብ ጠባቂ ከቤኒን ፣ 2 አጥቂዎች ደግሞ ከካሜሩን አስፈርሟል፡፡ ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን የቀነሰው ከአማካይ ስፍራ በመሆኑ ባለው አጭር ጊዜ ተጠቅሞ የሳሳውን የአማካይ ክፍል እንዴት እንደሚያጠናክር አጠያያቂ ሆኗል፡፡

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ ቡና በሲቲ ካፕ ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡ አሰልጣኝ ፖፓዲች ውድድሩ የቅድመ ውድድር ዝግጅታችን ላይ ጫና ይፈጥራል በሚል ላይሳተፉ እንደሚችሉ ተናግረው የነበረ ሲሆን አሁን ግን ለመወዳደር ከውሳኔ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡ ከሲቲ ካፑ በፊትም ከሲዳማ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኤሌክትሪክ ጋር የዝግጅት ጨዋታ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ያጋሩ