ሽመልስ በቀለ በአምበልነት የሚመራው ፔትሮጄት ስፖርቲንግ ክለብ ጋቶች ፓኖም የሚጫወትበት ኤል ግዋናን በግብፅ ፕሪምየር 8ኛ ሳምንት አሰተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
ባለሜዳው ፔትሮጀት በ4-2-3-1 አሰላለፍ የቀረበ ሲሆን ሽመልስ ከአጥቂ በስተጀርባ የ10 ቁጥር ሚና ተሰጥቶት ተጫውቷል። ለቡድኑም በርካታ እድሎችን የመፍጠር ኅላፊነት ሲወጣ ነበር። ጋቶች በበኩሉ በቡድኑ የ4-4-2 አሰላለፍ በመሃል አማካይነት ተሰልፎ ተጫውቷል።
ፔትሮጀቶች ኳስን አደራጅቶ በመጫወት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት በርከት ያሉ የግብ ማግባት ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ነገር ግን መልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው ያደረጉት ኤል ጎዋናዎች ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ ሆነዋል። በ15ኛው ደቂቃ የፔትሮጄት ተከላካዮች ወደ ሜዳው አጋማሽ ተጠግተው ሲያደርጉ የነበረውን ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ተጠቅሞ ኢስላም ሮሽዲ ረጅም ርቀት ብቻውን በመግፋት በፔትሮጄት መረብ ላይ ማሳረፍ ችለዋል። በ41ኛው ደቂቃ ደግሞ በድጋሚ ኢስላም ሮሽዲ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ በማስቆጠር ኤል ጎውናዎች የመጀመሪያውን አጋማሽ 2-0 በሆነ መሪነት ማገባደድ ችለዋል።
በዚህ አጋማሽ ሽመልስ ሶስት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችል በተለይም በ44ኛው ደቂቃ የሞከራት እና የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችው የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።
ፔትሮጀቶች ጨዋታውን በ10 ተጫዋች እንዲጨርሱ በተገደዱበት ሁለተኛ አጋማሽ ሽመልስን በአጥቂነት ተጠቅመዋል። ኤል ግዋናዎች በበኩላቸው አሰላለፋቸውን ወደ 4-2-3-1 በመቀየር ኳስን በማረጋጋት እና በመቆጣጠር ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ፔትሮጀቶች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም በ60ኛው ደቂቃ ሽመልስ ከኤል ግዋናው ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ውጭ የሰደደው እና በ70ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ አክርሮ የመታውና ቋሚ የመለሰበት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ሽመልስ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ከቀኝ ክንፍ መሬት ለመሬት የተሻገረለትን ኳስ በቀላሉ አስቆጥሮ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም ቡድኑን ከሽንፈት ሳይታደግ ቀርቷል።
በጨዋታው ኤል ጎውና በፔትሮጄት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደበት መሆኑን ተከትሎ ጋቶች ፓኖም እምብዛም ኳስን ሳይገኝ ቀርቷል። ኳሶችን በማስጣል እና ክፍተቶችን በመድፈን ግን ለቡድኑ ውጤታማነት የራሱን ድርሻ መወጣት ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ ኤል ጎውና ደረጃውን ወደ አምስተኛ ሲያሳድግ ፔትሮጄት ወደ 11ኛ ተንሸራቷል።
ከዚህ ጨዋታ ቀጥሎ እየተተከናወነ የሚገኘው ዑመድ ኡኩሪ የሚገኝበት ስሞሀ እና የቀድሞው የጅማ አባ ጅፋር አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ የሚጫወትበት ኢስማይሊ 65 ደቂቃዎችን ያስቆጠሩ ሲሆን ስሞሀ 2-1 እየመራ ይገኛል።