ኢትዮ ኤሌክትሪክ 11 አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም አስር የታዳጊ ተጫዋቾችን በዋናው ቡድኑ ውስጥ አካቶ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ነገ ወደ አዳማ ይጓዛል፡፡
በአዲስ ስራ አመራር ቦርድ የቀድሞ ታሪኩን ለመመለስ መልካም ጅምሮችን እያሳየ ያለው የኢትዮ ኤሌክትክ ስፖርት ክለብ ከአስራ አምስት ዓመት በታች እስከ ዋናው የወንዶች እና የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የተመደቡ አሰልጣኞችን የፊርማ ስነ ስርዐት ደጋፊዎች ፣ አሰልጣኞች ፣ የቡድን መሪዎች ፣ የክለቡ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማከናወኑ ይታወሳል፡፡
የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች እንደማያስተናግድ በይፋ ያሳወቀው ክለቡ ከነገ ጀምሮ ደግሞ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ አዳማ ያቀናል። በዝግጅቱ ተካፋይ ከሆኑት 31 ተጨዋቾች መካከል በፕሪምየር ሊጉ ሲያገለግሉ የቆዩት አዲስ ነጋሽ ፣ በኃይሉ ተሻገር ፣ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ተክሉ ተስፋዬ ፣ ጥላሁን ወልዴ ፣ ዮሀንስ በዛብህ ፣ ምንያህል ይመር ፣ ስንታየሁ ሰለሞን ፣ ስንታየሁ ዋልጮ እና ኦኛ አምኜ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ አምና በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ወ/አማኑኤል ጌቱን ጨምሮ አቤል አክሊሉ ፣ ጌታሰጠኝ ሸዋ ፣ አማኑኤል አዲሱ ፣ አማኑኤል ተስፋዬ ፣ ሀቢብ ከማ ፣ ዮሀንስ ተስፋዬ ፣ ሙባሪክ ከድር ፣ ሲሳይ አቡሌ እና እሸቱ ተሾመን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ወስዷል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡን ጨምሮ ውላቸውን ያጠናቀቁ እና የውል ማፍረሻ የከፈሉ በርካታ ተጫዋቾችን የለቀቀው ክለቡ በዝውውር መስኮቱ ሲሳተፍ ቆይቷል። በዚህ መሰረትም ሐብታሙ ረጋሳ ፣ ኢብራሂም ሁሴን ፣ ተስፋዬ ሽብሩ እና ኄኖክ መሀሪን ከሰበታ ከተማ ፤ ሚካኤል በየነ ፣ ቢኒያም ትዕዛዙ እና ሀብታሙ መንገሻን ከኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ወንድወሰን ገረመውን ከወላይታ ድቻ ፣ አቡበከር ደሳለኝን ከቡራዩ ከተማ ፣ አቡበከር ካሚልን ከየካ ክፍለከተማ ፣ ኤፍሬም ወንድወሰንን ከኢትዮጵያ ቡና አስፈርሟል።
ክለቡ በጥቅሉ አስር ከወጣት ቡድን ፣ አስር ነባር እና አስራ አንድ አዳዲስ ፈራሚዎች በድምሩ 31 ተጫዋቾችን ይዞ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ልምምዱን እንደሚያከናውን ይጠበቃል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 11 ቀን በሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ እንዳቀደም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።