የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በነገው እለት እንደሚከናወኑ ሲጠበቁ የ2010 የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሊያደረግ የተያዘለትን መርሐ ግብር እንደማያከናውን ክለቡ አረጋግጧል።
የጅማ አባ ጅፋር ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ዳምጠው ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት የ2010 ኢትዮጵያ ዋንጫን በ2011 ማከናወን በክለቡ እቅድ ውስጥ እንደሌለ እና የውድድር ዘመኑ ዝግጅት አካል እንዳልሆነ ገልፀው የነገውን ጨዋታ እንደማያከናውኑ ተናግረዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ውሳኔውን ተከትሎ በ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ አንድም ጨዋታ ያልተጫወተ ክለብ ሆኗል። በመጀመርያው ዙር ደደቢት ራሱን በማግለሉ በፎርፌ ወደ ቀጣይ ዙር ሲያልፍ በሩብ ፍፃሜው ኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ ባለመገኘቱ በተመሳሳይ በፎርፌ ለግማሽ ፍፃሜ ማለፉ የሚታወስ ነው።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና አወት ገብረሚካኤል እና ዲዲዬ ለብሪን ለማስፈረም መቃረቡ ታውቋል። ተጫዋቾቹ ከኤሌክትሪክ መልቀቂያቸውን ከወሰዱ ዛሬ ሊፈርሙ ይችላሉም ተብሏል። እንደ ስራ አስኪያጁ አቶ እስከዳር ገለፃ ከሆነ ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የተለያየው ያሬድ ዘውድነህን ጨምሮ ስምንት ተጫዋቾች (ስድስቱ ከውጪ) በሙከራ ጊዜ ላይ ሲሆኑ ከሁለት እስከ ሶስት ተጫዋቾች ሊፈርሙ ይችላሉ።