አዳማ ከነማ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ይሳተፋል

ሊጀመር ከ2 ሳምንት ያነሰ ጊዜ የቀረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ አዳማ ከነማ ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆኑን የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዘንድሮው ውድድር ላይ እንዲካፈሉ ጥያቄ ያቀረበላቸው ክለቦች አዳማ ከነማ እና ወላይታ ድቻ ሲሆኑ አዳማ ከነማ ፍቃደኛነቱን ሲገልፅ ወላይታ ድቻ እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱን የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ዮናስ ሃጎስ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ከነሃሴ 22 እስከ ጥቅምት 7 በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረገው ውድድር የምድብ ድልድል መስከረም 18 ወይም 19 የሚወጣ ሲሆን የስፖንሰር ሺፕ ጉዳዮችም በእለቱ ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አምና በካስቴል ቢራ ስፖንሰርነት የተካሄደው ውድድር በዚህ አመት በአምበር ቢራ ስፖንሰር እንደሚደረግ ቢነገርም ፌዴሬሽኑ ከማረጋገጥ ተቆጥቧል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ማቅማማቱ የተነገረ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ለመሳተፍ መወሰኑን ክለቡ አስታውቋል፡፡

አዳማ ከነማ ከብሄራዊ ሊጉ ካደገ ወዲህ ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ውድድሮች ማካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ሁለት ጊዜ በሴካፋ ክለቦች ዋንጫ ላይ ሲካፈል አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ወስኗል፡፡

ያጋሩ