ሶከር ሜዲካል| የሀገራችን የቅድመ ዝውውር ምርምራ ጉዳይ

ከእግር ኳስ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የህክምና ጉዳዮችን በምንዳስስበት በዚህ አምድ በዝውውር ወቅት መደረግ ያለበት ምርምራ በሀገራችን በበቂ ሁኔታ ያለመደረጉን ሁኔታ ተመርኩዘን የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች እና መፍትሄዎች የምናቀርብ ይሆናል። 

ከዚህ በፊት ባሰፈርነው ፅሁፍ (LINK) በዝውውር ወቅት የሚደረጉ የህክምና አይነቶችን እና ፋይዳቸውን ለመዳሰስ ሞክረናል። በሀገራችን ሊጎች የዝውውር ወቅት ከመሆኑ አንፃር በርካታ ዝውውሮች እየተደረጉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። እኛም በየጊዜው ዝውውሮች ሲጠናቀቁ ወደ አንባቢዎቻችን መረጃዎችን እያደረስን ነው። ሆኖም ግን ዝውውሮቹ ሲከናወኑ በሌሎች ሀገራት እንደምንመለከተው የህክምና ምርምራውን አጠናቆ ፈረመ የሚሉ መረጃዎች አይደርሱንም። እከሌ ይኸኛውን ክለብ ለቆ ለዚህኛው ፈረመ የሚሉ ዜናዎች እንጂ። 

በቅርቡም እንደታዘብነው ቶጓዊው አጥቂ ፎቪ አግዊዲ ለሐዋሳ ከተማ በፈረመ በሳምንቱ ከቡድኑ ጋር ተለያይቷል። አሉላ ግርማም ቅዱስ ጊዮርጊስን በመልቀቅ ጅማ አባጅፋርን በተቀላቀለ ማግስት ከቡድኑ ጋር መለያየቱ እየተነገረ ይገኛል። ለሁለቱም ተጫዋቾች ውላቸው በአጭሩ እንዲገታ ምክንያት የነበረው የጉልበት ጉዳት ነው። በ2010 የውድድር ዓመት ብዙ ገንዘብ ወጪ ተደርጎባቸው የተገዙ ተጫዋቾች በቂውን ግልጋሎት ሳይሰጡ ከክለቦቻቸው ጋር ሲለያዩ፤ ከነ ጉዳታቸው ሲጫወቱም አስተውለናል።

እንደዚህ ላሉት ሁኔታዎች መንስኤ ተብለው ሊነሱ የሚችሉ ምክንያቶች፡-

1) ክለቦች ለህክምና ዲፓርትመንት የሚሰጡት አናሳ ግምት

2) አንድ ክለብ የራሱ የሆነ ሐኪም እና ፊዝዮቴራፒስት ያለው አለመሆኑ

3) ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች አለመኖራቸው

4) የሚፈርሙ ተጫዎቾችን ያለፈ የህክምና ታሪክ አለማወቅ

5) አለማቀፋዊ የሆነ የዝውውር ስነ ስርአትን አለመከትል (ከህክምና ጀምሮ እስከ ውል መፈራረም)

በተጫዎቾች በኩልም የህመም ስሜትን እና ያለፈ ጉዳትን መደበቅ ይስተውላል። ይህም የመነጨው ጉዳቴ ከታወቀ ክለብ አላገኝም ከሚል ፍራቻ ነው።

መፍትሄው ምንድን ነው?

1) ክለቦች ተጫዋች ከማስፈረም በፊት ሙሉ የጉዳት ታሪኩን እና ጤንነቱን መጠየቅ እና ማወቅ አለባቸው

2) ብቃት ባለው ባለሙያ እና በዘመናዊ መሳሪያዎች የቅድመ ዝውውር ምርመራን ማከናወን

3) አንድ ተጫዋች የክለብ ንብረት እስከሆነ ድረስ ጉዳት በሚያጋጥመው ወቅት በቂ ድጋፍ፣ ክትትል እና እርዳታ ሊደረግለት ያስፈልጋል። ተጎድተሃልና መቀጠል አንችልም ብሎ ውልን ማፍረስ ትክክለኛ አሰራር አይደለም ።

4) ተጫዋቾችም ከሚያገኙት ገንዘብ ይልቅ ጤንነታቸው ስለሚበልጥ የሚሰማቸውን ህመም እና ጉዳት በማሳወቅ በቂውን ትክክለኛ እርዳታ ሊያገኙ ያስፈልጋል። በድብቅ የሚያዙ ጉዳቶች በጊዜ ሂደት ለከፋ ጉዳት (ኳስን እስማቆም ድረስ) ሊያጋልጡ ይችላሉ።

ብዙ ገንዘብ የሚፈስበት እግር ኳሳችን እና ብዙ በጀት የሚመደብላቸው ክለቦቻችን አሰራራቸውን ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ በማድረግ እና ትክክል ካልሆነ ልማዳዊ አሰራር በመላቀቅ ከጊዜው ጋር መራመድ አለባቸው። ዋናው ነገር ጤና እንዲሉ የተጫዋቾች ደህንነት ጉዳይ ችላ የሚባል ነገር አይደለም።


ከዚህ ቀደም በሶከር ሜዲካል ላይ የቀረበውን ፅሁፍ ከታች ተጭነው ያገኙታል።

የቅድመ ዝውውር ህክምና ምርመራ አስፈላጊነት