በ2010 ሳይጠናቀቅ ወደ 2011 የተሸጋገረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ መርሐ ግብር በነገው ዕለት በሀዋሳ ከተማ ስታድየም ተከናውኖ ወደ ፍፃሜ የሚሻገሩት ክለቦች ይለያሉ።
08:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ ይጫወታሉ። የ13 ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ቻምፒዮኑ መከላከያ ከሊግ ውድድር ይልቅ ለጥሎ ማለፍ የተፈጠረ እስኪመስል በተደጋጋሚ እስከመጨረሻው ከሚጓዙ ክለቦች ዝርዝር አይጠፋም። ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማን በመደበኛ ክፍለ ጊዜ ውጤት አሸንፎ የደረሰው ቡድን የነገውን ጨዋታ ካሸነፈ ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት የፍፃሜ ተፋላሚነቱን የሚያረጋግጥ ይሆናል። በሥዩም ከበደ እየተመራ በ2010 የውድድር ዓመት ሁለተኛ ዙር መሻሻል እንደማሳየቱ፣ በአዳዲስ ተጫዋቾች ተጠናክሮ እንደመቅረቡና ቁልፍ ተጫዋቾቹ ባለመልቀቃቸው ጥሩ የውድድር ዓመት ጅማሮ ሊያደርግ ይችላል።
ወልዲያ እና አርባምንጭን ጥሎ ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰው ኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ እያሳለፈ ከሚገኘው ጊዜ አንፃር ጥያቄዎች የተሞላ የውድድር ዓመቱን ነገ ይጀምራል። ክለቡ በርካታ ተጫዋቾቹን ለቆ በዛው መጠን በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች ባያመጣም እንደ ዋቴንጋ እና አልሀሰን ካሉሻ የመሳሰሉ የቡድኑን ደረጃ ሊጨምሩ የሚችሉ ተጫዋቾችን አካቷል። ቡድኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ እንደሆኑ የታመነባቸው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የመጀመርያ ሙሉ የውድድር ዓመታቸውን በጥሩ መንፈስ ለመጀመር ቡና ከ2000 ወዲህ ስኬታማ መሆን ያልቻለበትን ይህን ውድድር እንዲያሸንፍ መርዳት ይጠበቅባቸዋል።
ከጨዋታው ጋር በተያያዙ የቡድን ዜናዎች በኢትዮጵያ ቡና በኩል እያሱ ታምሩ እና አቡበከር ነስሩ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን በመከላከያ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ሲመራው በተመሳሳይ ኢንተርናሽናል ዳኞች የሆኑት ክንዴ ሙሴ እና ትግል ግዛው በረዳትነት ያጫውታሉ።
የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር እንደማይጫወት ያሳወቀበት የጅማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር በቅዱስ ጊዮርጊስ የፎርፌ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። ኢንተርናሽናል ዳኞች በላይ ታደሰ፣ በላቸው ይታየው እና ሽዋንግዛው ተባባል እንዲመሩ ተመድበው የነበሩ ዳኞች ናቸው።