በየዓመቱ ለቅድመ ዝግጅት ውድድር ይረዳ ዘንድ በሀዋሳ ከተማ የሚደረገው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ጥቅምት ወር ላይ መደረግ እንደሚጀምር የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቀጥሎ ረዘም ያለ ጊዜን ያስቆጠረው እና በፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል በየዓመቱ በደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን አስተናጋጅነት የሚከናወነው የደቡብ ክልል ካስትል ዋንጫ ከጥቅምት 1-10 በሀዋሳ እንደሚዘጋጅ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ አቶ ደመላሽ እንደገለፁት በክልሉ የሚገኙት ክለቦች ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ወላይታ ድቻን እና አዲስ አዳጊው ደቡብ ፖሊስን ጨምሮ ተጋባዥ ሁለት ክለቦችን በማካተት በ6 ቡድኖች መካከል የሚደረግ ሲሆን በዙር በሚደረግ ውድድር ድምር የነጥብ ብልጫ ያስመዘገበው ቡድን አሸናፊ ይሆናል። ከተጋባዦቹ መካከል ለኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጥሪ እንዳቀረቡና በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልግ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ከተገኘ ግን በምድብ ከፍሎ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በተያያዘዘ በየዓመቱ ለከፍተኛ ሊግ እና የአንደኛ ሊግ ተሳታፊ የክልሉ ክለቦችን የሚያሳትፍ ውድድርም በጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚደረግ ሰምተናል፡፡
ለሶስተኛ ዓመት የስያሜ ስፖንሰር በሆነው ካስቴል ቢራ ስም የሚከናወነው ውድድር ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን አምና አርባምንጭ ከተማ (ፎቶ) በፍፃሜው ሲዳማ ቡናን 1-0 በማሸነፍ የዋነረጫ ባለቤት መሆኑ ይታወሳል።