የከፍተኛው ሊግ ምድብ ሀ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ መድን ዋና እና ረዳት አሰልጣኞችን ቅጥር ፈፅሟል።
መድን አሰልጣኝ ደረጀ በላይን ካሰናበተ በኋላ በቀድሙ ኮከቡ ሀሰን በሽር እየተመራ የውድድር ዓመቱን በአቻ ብዛት ቁንጮ ሆኖ በሰንጠረዡ ወገብ አጠናቋል። ክለቡ ወደ ሊጉ ለመመለስ ቀደም ብሎ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን ለረጅም ጊዜ የቆየውና የአሰልጣኝ ቅጥር ጉዳይ 29 አሰልጣኞችን ካወዳደረ በኋላ በፀሎት ልዑልሰገድን ዋና አሰልጣኝ፣ ያሬድ ቶሌራን ደግሞ ምክትል ሆነው በአንድ ዓመት የስምምነት ውል ተሹመዋል።
ከ1999 ጀምሮ በበቆጂ ከተማ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ከተማ የሰሩት አሰልጣኝ በፀሎት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ከተለያዩ በኋላ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን በመያዝ ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በመድንም ተመሳሳዩን ስኬት አስመዝግበው ወደ ፕሪምየር ሊግ የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
የአሰልጣኝ በፀሎት ረዳት በመሆን የተሾሙት አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ ናቸው። በሴቶች እግርኳስ የአሰልጣኝነት ስራ የጀመሩት አሰልጣኝ ያሬድ የመድን ተስፋ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን፣ ለገጣፎ እና ወልቂጤ ከተማ ከተማ ከሰሩ በኋላ ወደ ለገጣፎ በድጋሚ ተመልሰው ክለቡን ወደ ከፍተኛ ሊግ በማሳደግ ጠንካራ ተፎካካሪ ማድረግ ችለዋል።