በአንጋፋው የድሬዳዋ ስታድየም የሜዳውን ጨዋታዎች የሚያደርገው ድሬዳዋ ከተማ በእድሳት አለመጠናቀቅ ምክንያት የመጀመርያዎቹ የሜዳው ጨዋታዎቹን ሐረር ላይ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የ1968 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የድሬዳዋ ስታድየም ከ2010 የውድድር ዓመት መጠናቀቅ በኋላ በእድሳት ላይ የሚገኝ ሲሆን ሜዳው ዝናብ እንዳይቋጥር ተደርጎ በዘመናዊ መልኩ እየተሰራ እንደሆነና የጠጠርና የአሸዋ የማንጠፍ ስራው እንደተጠናቀቀ መስከረም መጨረሻ አካባቢ አፈር ለብሶ ሳር መተከል እንደሚጀመር ክለቡ በፌስቡክ ገፁ ገልጿል። በዚህም ምክንያት የመጀመርያዎቹ አንድ ወይም ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን በሁለተኝነት ባስመዘገበው የሐረር ስታድየም እንደሚያከናውን አስታውቋል።
ሐረር ሲቲ በ2006 ወደ ከፕሪምየር ሊጉ ከወረደ በኋላ አንደኛ ሊግ ላይ የሚሳተፉት ሐረር አባድር እና ሐረር ሲቲ ጨዋታዎችን እያስተናገደ ይገኛል።
(ፎቶዎች – የድሬዳዋ ከተማ የፌስቡክ ገፅ)