በከፍተኛ ሊጉ የመለያ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ሽረ እንዳስላሴ ወደ ዝውውር እንቅስቃሴ ዘግይቶ በመግባት አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የ15 ተጫዋቾቹን ውል አድሷል።
ከሽረ አዲስ ፈራሚዎች መካከል ኢብራሂማ ፎፋና አንዱ ነው። አይቮሪኮስታዊው የመስመር አጥቂ በ2009 በኤሌክትሪክ ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢያመራም ከግማሽ ዓመት በኋላ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ያለ ክለብ ቆይቷል።
ሰለሞን ገብረመድህን ከወልዲያ ውጤታማ ያልሆነ የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ሽረን ተቀላቅሏል። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በመተሐራ ስኳር፣ ሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ንግድ ባንክ። ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በ2009 በፋሲል ከነማ ጥሩ ጊዜ ቢያሳልፍም አምና በወለዲያ አመዛኑን ጊዜ በጉዳት አሳልፏል።
ደሳለኝ ደበሽ ሌላው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነው። የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በአዳማ ከተማ የነበረው ኮንትራት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሽረ አምርቷል። የቀድሞው የሐረር ቢራ እና አዳማ ከተማ እንዲሁም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ዲሜጥሮስ ወልደስላሴም ወደ ሽረ አምርቷል።