የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ሲከናወን ፌደሬሽኑ ከቀድሞ አመታት በተለየ ውድድሩን ደማቅ ለማድረግ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ አስታውቋል። ፌደሬሽኑ በአመቱ የተለያዩ ውድድሮችን በከተማው ለማከናወን የሚረዳውን የኢኮኖሚ አቅም ከፍ ለማድረግ የሚጠቀምበት የሲቲ ካፕ ውድድር በአመቱ መጀመሪያ ሲያደርግ ዘንድሮም ከመስከረም 26 – ጥቅምት 11 ውድድሩን ለማከናወን ማቀዱን ቀደም ብሎ መግለፁ ይታወሳል።
በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፈለ የአዲስ አበባ ክለቦች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ ፌደሬሽኑ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ተጋባዥ ክለቦችን ለማብዛት የታሰበ ሲሆን እስካሁን በተጋባዥነት የታሰቡ ሶስት የሃገር ውስጥ እና አንድ የአፍሪካ ክለብ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተገልጿል። አዲሱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሃይለየሱስ ፍስሃ(ኢ/ር) ዛሬ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት ማረጋገጫ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉት ኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ እንዲሁም ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ኢትዮ ኤሌክተሪክ ከተማዋን በመወከል እንደሚሳተፉ ገልፀዋል። የውድድሩ የአምስት ጊዜ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን እስካሁን ማረጋገጫ እንዳልሰጠ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ ክለቡን በውድድሩ ተሳታፊ ለማድረግ ግን ድርድሮች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ክለቡ ውድድሩ በሚደረግበት ወቅት ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታ 9 ተጫዋቾችን ስለሚያጣ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በቂ የቡድን ስብስብ ስለማይኖረን ነው ብለው እንዳስረዷቸውም ጠቁመዋል።
ከከተማዋ ውጪ ያሉ ተጋባዥ ክለቦችን በተመለከተ ደግሞ አዳማ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ጅማ አባ ጅፋር በውድድሩ ለመካፈል ይፋዊ ማረጋገጫ እንደላኩ ተረጋግጧል። ከሶስቱ የሀገር ውስጥ ተጋባዥ ክለቦች በተጨማሪ ኳራ ዩናይትድ የተባለ የናይጄሪያ ክለብ በውድድሩ ተሳታፊ ለማድረግ እንደታሰበና ስራዎች እንደተጠናቀቁ ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
ይህ ክለብ የፊታችን ሰኞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ኃይለየሱስ የሆቴል እና የአየር ትራንስፖርት ወጪውን ራሱ ክለቡ እንደሚሸፍን ነገር ግን የሃገር ውስጥ ትራንስፖርት እና የልምምድ ሜዳ ወጪዎቹን ፌደሬሽኑ እንደሚሸፍን አስረድተዋል። አምና በተሻሻለው የውድድሩ ደምብ መሰረት ደግሞ ክለቡ የውድድሩ አሸናፊ ከሆነ እንደ ሌሎቹ ክለቦች ከሚገኘው የስታዲየም ገቢ በመቶኛ ተሰልቶ እንደሚሰጠው ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና ውድድሩን በቴሌቪዥን በቀጥታ ለማስተላለፍ ከዋልታ ቲቪ ጋር በመርህ ደረጃ መስማማታቸው የተነፀገለፀ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረግ ይፋዊ የፊርማ ስነ ስርዓት ጉዳዩ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ወይም ሀሙስ ደግሞ የውድድሩ የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ሆቴል እንደሚከናወን ለማወቅ ተችሏል።