ከተለያዩ የክለቡ አካላት የተውጣጣው የጉብኝት ቡድን በሁለት ባለውለታዎቹ መኖሪያ ቤት ተገኝቶ ስጦታዎችን አበርክቷል።
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች ታሪክ ውስጥ በተጨዋችነት ፣ በአሰልጣኝነት ፣ በደጋፊነት እንዲሁም በአስተዳደር ቦታዎች ልልይ በርካታ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦች እንደሚገኙ ይታወቃል። ሆኖም እነዚህ ግለሰቦች በተለይም ከመድረኩ ሲርቁ እውቅና ሳይሰጣቸው ሲዘነጉ ብሎም ሲረሱ ይስተዋላሉ። በርግጥ ከቅርብ አመታት ወዲህ የደጋፊ ማህበራት መጠናከር እና በማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት የመሳተፍ ልምድ መምጣት በዚህም ረገድ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይታመናል። ነገር ግን ክለቦችም እንደተቋም በራሳቸው ተነሳሽነት ጀግኖቻቸውን መለስ ብሎ መመልከት እና መደገፍም ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ረገድ ለብዙዎች ትምህርት ሊሆን በሚችል መልኩ አዲሱ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ቦርድ አመራር ከትናንት በስትያ በዕለተ ደመራ በሁለት የክለቡ ባለውለታዎች መኖሪያ ቤት በመገኘት ‘ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ለሰራችሁት ውለታ ማካካሻ ሊሆን ባይችልም ማስታወሻ’ በሚል ርዕስ የምስጋና ፕሮግራም አከናውኗል። በዕለቱ ከስፖርት ክለቡ ፅህፈት ቤት ፣ ከቦርድ አመራሩ ፣ ከእግር ኳስ ክለቡ አስተዳደር ፣ ከቴክኒክ ዳይሪክተሮች እንዲሁም ከደጋፊዎች የተውጣጣ ስብስብ ነበር ከረፋድ 8፡00 ጀምሮ ወደ ባለውለታዎቹ ቤት ጉዞ ያደረገው።
የቡድኑ የመጀመሪያ መዳረሻም በየካ አባዶ የሚገኘው የቀድሞው አሰልጣኝ ወንድምአገኝ ከበደ መኖርያ ቤት ነበር። አሰልጣኝ ወንድምአገኝ ከክለቡ ታሪካዊ ቡድኖች መካከል በ1985 ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን መሆን የቻለውን ቡድን በአሰልጣኝነት መምራታቸው የሚታወስ ነው። ይህንን ምክንያት በማድረግም አሰልጣኙ ከወቅቱ ቡድናቸው ጋር ሆነው የሚያሳይ እና ‘የ1955 እና 1986 ምርጥ እና ታላቅ አሰልጣኝ’ የሚል ትልቅ ምስል ፣ የማስታወሻ ዋንጫ ፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ደግሞ የአስር ሺህ ብር ቼክ ተብርክቶላቸዋል። አሰልጣኙ ከእንባቸው ጋር እየታግልሉ በሰጡትም አስተያየት ክለቡ ለሰሩት ስራ እውቅና በመስጠቱ ወገን እንዳላቸው እና እንዳልተረሱ እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው ገልፀው የክለቡን አመራሮች አመስግነዋል።
በክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ የተመራው የዕለቱ ቡድን በቀጣይ ከየካ አባዶ በመነሳት ወደ ሳሪስ አቅንቷል። በክለቡ ውጤታማ ዓመታትም ሆነ እጅግ ወርዶ በታየባቸው ጊዜያት ቀይ አርማቸውን እንደለበሱ ከተለምዶው የአዲስ አበባ ስታድየም ቦታቸው ላይ የማይጠፉት የአቶ በቀለ ሄኔ (ኮረንቲ) መኖሪያ ቤት ደግሞ የመጨረሻ መዳረሻው ሆኗል። ከ40 አመታት በላይ ክለባቸውን ያለድካም ሲደግፉ የቆዩት አቶ በቀለ አዲሱ አመራር በዚህ መልኩ ቦታ ሰጥቶ ስላከበራቸው አመስግንው ወደፊትም ከክለቡ የሚለያቸው እንደሌለ በጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆነው ገልፀዋል። እንደ አሰልጣኝ ወንድማገኝ ሁሉ አቶ በቀለም የማስታወሻ ዋንጫ ፣ ዘወትር የማይለያቸውን የድጋፍ አርማ አጥልቀው የተነሱት እና ‘የውጤት መጥፋት ያላጠፋው ታላቅ ሰው’ የሚል ምስል እና የአስር ሺህ ብር ቼክ ከጉብኝት ቡድኑ ተቀብለዋል። እንደ ክለቡ ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ኢሳያስ ደንድር ሀሳብ ክለቡ በተመሳሳይ ጅግኖቹን ማሰቡን የሚቀጥል ሲሆን ከቀናት በኋላም የታላቁ አሰልጣኝ ሀጎስ ደስታ ቤተስቦችን የመጎብኘት ሀሳብ እንዳላቸው ታውቋል።