ሪፖርት | መከላከያ የ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ ቻምፒዮን!

የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ዋንጫ በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ያደረጉህ ጨዋታ መደበኛው ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ በመጠናቀቁ በመለያ ምቶች መከላከያ 3-2 በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችሏል። 

መከላከያ ከ3 ቀናት በፊት በግማሽ ፍፃሜው ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 ያሸነፈውን ቡድን ሙሉ ለሙሉ ለዛሬው ጨዋታ ሲጠቀም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በመለያ ምቶች ካሸነፈበት ጨዋታ ታደለ መንገሻን በተጠባባቂ ወንበር በማስቀመጥ ለአቡበከር ሳኒ የመጀመርያ ተሰላፊነት እድል ሰጥቷል። 

በበላይ ታደሰ ዳኝነት 09:15 ላይ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ እጅግ የተቀዛቀዘ እና ወጥ ያልሆነ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ነበር። መከላከያዎች በቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ያለመ እንቅስቃሴያቸው ስኬታማ ያልነበረ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመከላከያ ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተት ለመጠቀም ጥረት አድርገው ጥቂት የግብ እድሎች ፈጥረዋል። በ12ኛው ደቂቃ ጌታነህ ለአቤል አሳልፎለት ጥሩ እድል ፈጥሮለት አበበ ቀድሞ ያወጣበት፣ በ36ኛው ደቂቃ አቤል ከሳጥኑ ጠርዝ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ40ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ የሞከረውና ይድነቃቸው ኪዳኔ የመለሰበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ናቸው። 

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው በተሻለ የጎል ሙከራዎች የታዩ ሲሆን በተለይ በመከላከያ በኩል ምንይሉ ወንድሙ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል ቀርቷል። በ53ኛው ደቂቃ ተመስገን ጀርባውን ለተከላካይ ሰጥቶ በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸለትን ኳስ መትቶ ኢላማውን ስቶ ሲወጣበት በ62ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ከመስመር ያሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢገኝም በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ለዓለም ይዞበታል። በ68ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ መትቶ ለጥቂት የወጣበት ኳስም ከምንይሉ ሙከራዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። በዚህ አጋማሽ ጌታነህ ከርቀት ከሚመታቸውና ኢላማቸውን ከሳቱ ሙከራዎች ውጪ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የጠራ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። 

ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ በቀጥታ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አስቻለው ታመነ እና ጋዲሳ መብራቴ ምቶቹን ወደ ግብነት ሲቀይሩ በኃይሉ አሰፋ በግቡ አናት ወደላይ ሰዶታል። ናትናኤል ዘለቀ እና ጌታነህ ከበደ የመቷቸውን ኳሶች ደግሞ ይድነቃቸው ኪዳኔ መልሶባቸዋል። በመከላከያ በኩል ምንይሉ ወንድሙ፣ ተመስገን ገብረኪዳን እና አበበ ጥላሁን (የማሸነፍያውን) ሲያስቆጥሩ ሽመልስ ተገኝ በግቡ አግዳሚ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ደግሞ በለዓለም ብርሀኑ ተመልሶባቸዋል። በዚህም መከላከያ 3-2 አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። 

14 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ባለ ሪከርድ የሆነው መከላከያ የዋንጨጫ ባለቤት መሆኑን ተከትሎ ህዳር ላይ የሚጀመረው የ2018/19 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።