ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገውና በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ የሶስት ተጫዋቾችን ዝውውር በዛሬው እለት አጠናቋል። ሳምሶን መሉጌታ፣ መስፍን ኪዳኔ እና ፍርዳወቅ ሲሳይም ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል።
በ1991 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ እስከ 2003 ድረስ በክለቡ ተጫውቶ ያሳለፈው ሳምሶን የመጨረሻዎቹን ሶስት አመታትም ቡድኑን በአምበልነት መርቷል። በንግድ ባንክ ለሁለት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ መድን ደግሞ እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ መጫወት ችሏል። በደቡብ ፖሊስ ለአንድ የውድድር ዓመት ለመጫወት የተስማማው ሳምሶን ከአንድ ወር በኋላ የሚጀመረው የ2011 ፕሪምየር ሊግ አንጋፋው ተጫዋች እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ፍርዳወቅ ሲሳይ ወደ ሀዋሳ የመለሰውን ዝውውር አድርጓል። በሀዋሳ ከተማ በ2006 ከታዳጊ ቡድን ባደገበት ዓመት ተስፈኛ እንቅስቃሴን ሲያሳይ የነበረው ፍርዳወቅ ያለፉትን ሁለት የውድድር አመት የተጠበቀውን ያህል መሆን ሳይችል ቀርቶ በ2010 የውድድር ዘመን በአዳማ ከተማ ለስድስት ወራት ያክል ቆይታን ካደረገ በኋላ አሁን ደግሞ ደቡብ ፖሊስን መቀላቀል ችሏል።
ሌላኛው ፖሊስን የተቀላቀለው አማካዩ መስፍን ኪዳኔ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን 2000 ላይ ካደገ በኃላ በክለቡ ጥሩ ጊዜን አሳልፎ ወደ ደደቢት በ2006 አምርቶ ሁለት ዓመታትን በሰማያዊዎቹ ቤት ካሳለፈ በኃላ በመከላከያ እንዲሁም በ2010 ግማሽ ዓመት በወልዲያ ተጫውቷል።
ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች ጎን ለጎን የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል በማራዘም ላይ ሲገኝ ኤሪክ ሙራንዳ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በክለቡ የሚያቆየውን ውል ማኖሩን ክለቡ ገልጿል። በተጨማሪም 5 ተጫዋቾች ሙከራ ላይ ሲሆኑ በቀጣይ ቀናት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉትን እንደሚያስፈርም ታውቋል።