የኢትዮጵያ ዋንጫ የ2010 ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመከላከያ በመለያ ምቶች ተሸንፎ ዋንጫውን ከማጣቱ በተጨማሪ ከ2006 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ ውድድር እንደማይካፈል አረጋግጧል።
አሰልጣኝ ፒንቶ ከዛሬው የፍፃሜ ጨዋታ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ስለ ጨዋታው ይህን ብለዋል። ” ጨዋታው ሁለት መልኮች ነበሩት። በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ ከመከላከያዎች የተሻልን ነበረን። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ መከላከያዎች ከኛ ተሽለው ተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ነበር። በ90 ደቂቃው የተመዘገበው የአቻ ውጤት ጨዋታውን አይገልፀውም። ምክንያቱም ሁለታችን ጥሩ ብቃት እና እንቅስቃሴ ስላሳየን። በግሌ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን ስነረፈጥር ነበር፤ ባሳየነው እንቅስቃሴም ተደስቻለው። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ቡድናችን መጠነኛ ችግሮች ነበሩበት። በተለይ የአማካይ ክፍሉ እና የአጥቂ ክፍሉን የቅንጅት ክፍተቶች ነበሩበት። ይህ ደግሞ የሆነው አብዛኞቹ ተጨዋቾቼ ለብሄራዊ ቡድን ግዳጅ በመሄዳቸው አብረውን ስላልነበሩ ነው። እነሱ ከመጡ በኋላ ደግሞ ለአንድ ሳምንት ብቻ ነው ልምምዶችን በተሟላ ሁኔታ ያከናወነው። እነዚህም ተጨዋቾች አሁንም ተመልሰው ወደ ብሄራዊ ቡድን ስለሚሄዱ ነገሮችን እነሱ ከተመለሱ በኋላ ለቀጣይ ጨዋታዎቻችን ለማስተካከል እንሞክራለን። በአጠቃላይ ግን በጨዋታው ሁለታችንም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፤ በመለያ ምቶቹ ግን መከላከያዎች ከኛ የተሻሉ ነበሩ ስለዚህ ማሸነፋቸው ይገባቸዋል። እንኳን ደስ አላችሁም ማለት እፈልጋለው። ”
ቫዝ ፒንቶ ዋንጫውን አለማንሳታቸውን ተከትሎ በክለቡ ስለሚኖራቸው ቆይታ ተጠይቀው በክለቡ ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል። ” በክለቤ በጣም ደስተኛ ነኝ። ገና ጎልማሳ ስለሆንኩም ወደፊት ከፍተኛ እቅዶች አሉኝ። ነገር ግን አሁን ባለሁበት ክለብ ገና የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት ስላለኝ የተሻለ ነገር ለማምጣት ከነገ ጀምሮ ስራዬን አጠናክሬ እቀጥላለው። “