በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ ረፋድ ላይ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በካፒታል ሆቴል እና ስፓ በተሰጠው መግለጫ ብሔራዊ ቡድኑ መስከረም 30 በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ስለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅት፣ ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (FIFA) ለንደን ላይ ስላከናወነው ኮንፍረንስ እና ብሔራዊ ቡድኑ የእድሜ ልክ የቀይ መስቀል አባል ስለመሆኑ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በቦታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ (ኢንስትራክተር) እና የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ተገኝተው መግለጫውን የሰጡ ሲሆን ከጋዜጠኞችም ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሾች ተሰተዋል። 4:15 ሲል በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የመክፈቻ ንግግሩ የተጀመረው መግለጫው አሰልጣኙ ከሴራሊዮኑ የድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልስ በኋላ ከሚዲያ ጋር ተገናኝተው ቃለ ምልልሶችን ማድረግ ያልቻሉት ሙሉ ትኩረታቸውን በቡድኑ ዝግጅት ላይ ለማድረግ አስበው እንደሆነ በቦታው ለተገኙ ጋዜጠኞች በማስረዳት ዛሬ በሚፈለገው ጉዳይ ላይ ምላሽ እና ማብራሪያ ለመስጠትና እንደተዘጋጁ በመጥቀስ የዕለቱ የመግለጫ አጀንዳዎችን አስተዋውቀዋል።

አሰልጣኙ አጀንዳዎቹን ካስተዋወቁ በኋላ በቀጥታ ወደ ጥያቄዎችን እንዲጠይቋቸው ለጋዜጠኞች እድሎችን የሰጡ ሲሆን ከጋዜጠኞች በአጀንዳዎቹ እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል።

በመጀመሪያ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ የቀይ መስቀል አባልነት ምዝገባ አስመልክቶ ለተነሳላቸው ዝርዝር ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አሰልጣኙ ጉዳዩ መልካም ነገር መሆኑን አስረድተዋል። “ብሄራዊ ቡድኑ ለቀይ መስቀል አባል መሆኑ በጣም መልካም ነገር ነው። አንደኛ በኛ በኩል የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ከመጫወት ባለፈ ሃላፊነት የሚሰማቸው ተጨዋቾች መሆናቸውን ማሳወቅ እንዳለባቸው በማመናችን ያደረግነው ነገር ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ በሰብዓዊ እና በተቀደሰ ነገር ላይ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾቹ መሳተፋቸው እንዳለባቸው በመረዳታችን ነው የእድሜ ልክ የአባልነት ምዝገባውን ያከናወነው። ዋናው ነገር ግን ቀይ መስቀል በሜዳ ላይም ተጨዋቾቹ ሲጎዱ ለመርዳት የሚጥሩት በጦርነትም ላይ ሰዎች ሲቆስሉ የሚያክሙት ስለሆኑ እነሱን መርዳት እንዳለብን በማመናችን ነው። ስለዚህ ለዚህ ትልቅ ተቋም አባል መሆን ለተለያዩ ተፈጥሮዋዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንደመድረስ ስለምንቆጥረው አባልነቱን ተቀብለነዋል።” በማለት ከዚህ በኋላ ለሚመጡት ብሔራዊ ቡድን አባላት እንደ አርያነት ለመታየት መስማማታቸው ጨምረው አስረድተዋል።


በመቀጠል አሰልጣኙ ስለ ኬንያው ጨዋታ እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚከተለውን ብለዋል። “በሁለተኛው የምድቡ ጨዋታዎች ኬንያ ጋናን በማሸነፏ እና እኛም ሴራሊዮንን በማሸነፋችን ሁላችንም ለአፍሪካ ዋንጫው ያለንን ለማለፍ እድል እኩል አድርጎታል። ከሴራሊዮኑ ጨዋታ በኋላ ቡድኑ ለጥሎ ማለፍ በነበሩ ጨዋታዎች እንዲበተን ተደርጓል።ነገር ግን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ጨዋታው ወደሚደረግበት ባህር ዳር አምርተን ልምምዳችንን እንጀምራለን። ዛሬ ባህር ዳር እንደገባን ከሪከቨሪ ጋር የተያያዙ ስራዎችን እንሰራለን። ከነገ ጀምሮ ግን እስከ ጨዋታው እስከሚደረግበት እለት ድረስ ሰባት መደበኛ ልምምዶችን ሰርተን ለጨዋታው ለመዘጋጀት እንሞክራለን።” ብለዋል።

አሰልጣኙ ጨምረውም ስለ ዝግጅት ጊዜ ማጠሩ ለተነሳላቸው ጥያቄ ደግሞ ይህንን ብለዋል። “የዝግጅት ጊዜ ማጠሩ፣ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በመሃል መግባታቸው እና የፕሮግራም አጠቃቀም ስህተት እንደ ችግር ሊነሱ ይችላሉ። ምክንያቱም ስብስቡ አዲስ እንደመሆኑ እና ከዚህ ቀደም ቡድኑ ለረጅም ወራት ተበትኖ እንደመቆየቱ ረዘም ያለ ጊዜ ቢኖረን በርከት ያሉ ስራዎችን ለመስራት እንችል ነበረ። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ከዚህ በኋላ እንዳይደገም እና ብሄራዊ ቡድኑ የራሱ የሆነ ካላንደር እንዲኖረው ከብሄራዊ ፌደሬሽናችን ጋር እየሰራን ነው ያለነው። ይህ ደግሞ ከባድ አይደለም የፊፋ እና ካፍ ካላንደር ከአመት በፊት ስለሚታወቅ በዛ መሰረት እቅዳችንን ከሀገር ውስጥ ውድድሮች ጋር አጣጥመን እናወጣለን።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዛሬ ከሰዓት ቡድኑ ወደ ባህር ዳር ሲያቀና በጥሎ ማለፉ ጨዋታዎች እና ጉዳቶች ምክንያት አስቻለው ታመነ፣ በኃይሉ አሰፋ እንዲሁም ሳላዲን በርጌቾ ከስብስቡ ጋር አብረው እንደማይጓዙ ተገልፃል። ስለ ሳልሃዲን ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡት አሰልጣኙ ለኬንያው ጨዋታ ተጨዋቹ ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ የሜም አር አይ(MRI) ምርመራ ዛሬ እንደሚደረግለት ገልፀው በህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ በሚመጣው ውጤት መሰረት ቡድናቸውን እንደሚቀላቀል ካልሆነ ግን ለሌሎች ተጨዋቾች ጥሪ በማቅረብ ለጨዋታው ዝግጅታቸውን እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።


ከአሰልጣኙ ማብራሪያ በኋላ መድረኩን በመረከብ ገለፃዎችን ያደረገው የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ሲሆን በሜዳችን በምናደርገው የኬንያ ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ አስረድቷል። “እኛ መጀመሪያ አቅደን የተነሳነው በሜዳችን የምናደርጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች ለማሸነፍ ነው። ነገር ግን በዝግጅታችን መሀል የገባው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በመጠኑ ተፅኖ ሊያመጣብን ይችላል። ምክንያቱም በጥሎ ማለፉ ላይ ሁሉም ተጨዋቾች ስላልተጫወቱ ሁላችንም ተመሳሳይ የአካል ብቃት እና የትንፋሽ ደረጃ ላይ እንዳንሆን ያደርገናል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ መጠነኛ ተፅዕኖ ሊያሳርፍብን ይቻላል ነገር ግን በሴራሊዮን ላይ ያስመዘገንነው ውጤት ሊደግፈን እና ሊያነሳሳን ይችላል።” በማለት ሃሳቡን አካፍሏል።
ከጌታነህ አስተያየት በኋላ መድረኩን በድጋሚ የተረከቡት አሰልጣኙ በሴራሊዮኑ ጨዋታ ላይ ስለታዩ ችግሮች እና ጠንካራ ጎኖች ገለፃ ሰተጥዋል። ብሄራዊ ቡድኑ በሴራሊዮኑ ጨዋታ ሲከተለው ስለነበረው የጨዋታ ዘይቤ መደሰታቸውን እና የስራቸው ውጤት መሆኑንም አስረድተል። አሰልጣኝ አብርሀም ኳስን ተቆጣጥሮ ስለመጫወታቸው ሲናገሩ በልምምድ ሜዳ ላይ ጠንካራ ስራዎችን በመስራታቸው ያመጡት ነገር እንደሆነ አፅኖት ሰጥተው ያስረዱ ሲሆን በተለይ ኳስን ከግብ ጠባቂው ሳምሶን ተጀምሮ በሂደት እንዲሄድ ለማድረግ በልምምድ ሜዳ መስራታቸውን ተናግረው በቀጣይም ይህንን እንደሚቀጥሉበት ገልፀዋል።

በመጨረሻም ፊፋ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስላከናወነው ኮንፍረንስ ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡት አሰልጣኙ በኮንፍረንሱ ከፍተኛ እውቀቶችን እንዳገኙ በመግለፅ በህዳር ወር በሀገራችን ለሚገኙ አሰልጣኞች ከማነቃቂያ ትምህርቶች ጋር አይያዞ በኮንፍረንሱ የተገኙትን እውቀቶች ለማካፈል  እንዳሰቡ ገልዋል።

አሰልጣኙ ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉም በቀጣይ ለብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ወይንም ተስፋ ቡድን ለማቋቋም ስራዎችን እንደሚሰሩ የገለፁ ሲሆን በተለይ ለ2020 የቻን ውድድር ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት እንደሚጥሩ አስረድተዋል።