የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለ13ኛ ጊዜ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ከቀደሙት ዓመታት የተለየ ለማድረግ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት ውድድሩን በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በመስማማት ይፋዊ የፊርማ ስነስርዓት ተከናውኗል።
ሁለቱ አካላት ድርድሮችን ቀደም ብለው መጀመራቸው ከዚህ ቀደም ሲገለፅ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ድርድሮቹ ፍሬ አፍርተው ዛሬ ከሰዓት ቴሌቪዥን ጣቢያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ይፋዊ የፊርማ ስነስርዓት ተከናውኗል። በዚህም መሰረት መስከረም 26 የሚደረገውን የመክፈቻ ጨዋታ፣ የተመረጡ የሁለቱም ምድቦች ሁለተኛ ጨዋታዎች፣ ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች እና ጥቅምት 11 የሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ በቲቪ ለማስተላለፍ ሁለቱ አካላት ተስማምተዋል።
ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኩል ስምምነቱን የፈረሙት አቶ ኃይለየሱስ ፍስሃ (ኢ/ር) ስምምነቱ ሌሎች ውድድሮችም በቴሌቪዥን እንዲተላለፉ መንገዱን ለመጥረግ እንደሆነ እና የውድድሩን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀው ስታዲየም መግባት የማይችሉ የስፖርት ቤተሰቦች በያሉበት ሆነው ጨዋታዎችን እንዲከታተሉ ታልሞ እንደሆነ ጨምረው ገልፀዋል።
ከመስከረም 26 – ጥቅምት 11 በሚደረገው ውድድር እስካሁን ሰባት ክለቦች ( ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መከላከያ፣ ጅማ አባጅፋር፣ አዳማ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ፣ ኳራ ዩናይትድ) በውድድሩ ለመሳተፍ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የገለፁት ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት የናይጄሪያው ክለብ ኳራ ዩናይትድ ነገ ምሽት ወደ አዲስ አበባ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ማረጋገጫ ከሰጡ ሶስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች ውጪ የውድድሩ የአምስትጊዜ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውድድሩ ላይ አልሳተፍ ማለቱን ተከትሎ ፌደሬሽኑ ሀሳብ የገባው ሲሆን ዛሬ ከሰዓትም ወደ ክለቡ ፅህፈት ቤት በማምራት ንግግሮች እንደተደረጉ ለማወቅ ተችሏል። ንግግሮቹ እስከተቻለው መጠን ድረስ ተደርጎ በጎ ምላሾች ከክለቡ የማይመጡ እና አንሳተፍም በሚለው አቋማቸው ከፀኑ ፋሲል ከነማን እንደ ስምንተኛ ክለብ በማምጣት ውድድሩ ለማከናወን እንደታሰበ ተሰምቷል።
በተያያዘ ዜና በውድድሩ ኮከብ ለሚሆኑ ተጨዋቾች የዋንጫ እና የተለያዩ ሽልማቶች እንደሚሰጥ ታውቋል።