በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረውን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም ከዛሬ ጀምሮ በተከታታይ ክፍሎች በድረ-ገፃችን ላይ እናቀርባለን። በዛሬው ክፍልም ረጅሙ የመጽሃፉ መቅድምን ክፍል እነሆ ብለናል፡፡ መልካም ንባብ!
መቅድም
በ2004ቱ የአውሮፓ ሀገሮች ዋንጫ ውድድር እንግሊዝ ሲውዘርላንድን 3-0 በነበረችበት ምሽት በፖርቹጋሏ ርዕሰ መዲና ሊዝበን ከሚገኙት ክፍለ ከተሞች አንዷ በሆነችው የባይሮ ኦልቶ መንደር ባለው የስፔናውያኑ ዝነኛ የእንቁላል ጥብስ መመገቢያና መዝናኛ ቦታ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጋዜጠኞች ተሰባስበዋል። ጋዜጠኞቹ በሰሜናዊ የስፔን ክልል ራዮሃ የሚመረተው ደረቁንና ቀዩን ወይን እየተጎነጩ ስዊድናዊው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስቬን ዮራን ኤሪክሰን ተለምዷዊው የ4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደርን የሙጥኝ ማለታቸው ትክክለኛ ውሳኔ ስለመሆኑ ይወያያሉ፡፡ “አሰልጣኙ በጨዋታ ወቅት በአንድ የጎንዮሽ መስመር የሚንቀሳቀሰው ዝርግ የአማካይ ክፍላቸውን ወደ <ዳይመንድ> የቦታ አያያዝ ቅርጽ ቢቀይሩ የተሻለ ያዋጣቸዋል፡፡” በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡም ነበሩ፡፡ ተጫዋቾች ያላቸው የተሰሚነት-ተጽዕኖ እና የመጀመርያ ተሰላፊ አማካዮችን የመምረጥ የመጨረሻ ውሳኔ በዝርግ ጎንዮሻዊ የሜዳ መስመር የሚደረደሩት አራት ተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ መዋቅር ላይ ያልተጠበቀ ለውጥ ለማምጣት አስገዳጅ ሁኔታን ይፈጥር ይሆን?
በዚያ የሞቀ ክርክር መሀል አንዱ እንግሊዛዊ የስራ ባልደረባችን ” ኡፍ! ተጫዋቾቹ ራሳቸው እስከሆኑ ድረስ ልዩነቱ ምንድን ነው? እርባና ቢስ ስለሆኑት ፎርሜሽኖች መጻፍም ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም ፡፡” ሲል ተቃውሞውን አሰማ፡፡ የሰውየው ድርጊት በፍጥነትና ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ንዴትን የመግለጽ ሒደት ነበር፡፡ በስካር ስሜት ሆኜ ‘እንደ እርሱ የሚያስቡ ሰዎች በፍፁም እግር ኳስን እንዲያዩ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡’ ብዬ በማሰብ እጄን ከፍ አድርጌ ልጎሽመው ሲቃጣኝ አንዲት አርጀንቲናዊት ጋዜጠኛ በትህትናና በብልሀት “እኛ ስለፎርሜሽን ብቻ እናወጋለን፡፡” ብላኝ እጄን እንዳወርድ አደረገችኝ፡፡ ” ፎርሜሽን ብቸኛውና ወሳኙ ነገር ነው፤ እንዲያውም ከፎርሜሽኖች ውጪ ስላሉ ነገሮች መፃፍ ረብ የለሽነት ነው፡፡” አለችኝ፡፡
ያ ቅጽበት የእንግሊዛውያኑ እግርኳስ አጨዋወት ላይ ትልቅ ጉድለት እንደሚታይ ያጋለጠ አጋጣሚ ሆነ፡፡ እግርኳስ ተጫዋቾችን ብቻ የሚመለከት ወይም ደግሞ የተጫዋቾች ችሎታ ላይ ብቻ የተመረኮዘ አይደለም፡፡ ይልቁንም ቡድኖች በጨዋታ የምልልስ ዑደት ውስጥ የሚያሳዩትን የሚዋልል መዋቅር፣ የመጫወቻ ቦታ ወይም ክፍተት፣ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚኖራቸውን የተሳካ ቦታ አያያዝ እንዲሁም በሚሰጣቸው ሚና የሚያደርጉትን አመርቂ እንቅስቃሴ የሚገልጽ ነው፡፡ (ምናልባትም ይህን ‘ታክቲክ’ የተሰኘ ጥቅል ሀሳብ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ የአጨዋወት ዘይቤና የፎርሜሽኖች ውህደት እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ አንደኛው የ4-4-2 ፎርሜሽን አይነት ከሌላኛው ተመሳሳይ ፎርሜሽን ጋር ልዩነት አለው፤ ስቲቭ ስቶን / የቀድሞው የአስቶን ቪላ እና ፖርትስማውዝ ተጫዋች / እና ሮናልዲንሆ እንደሚለያዩት ማለት ነው፡፡)
አርጀንቲናዊቷ ጋዜጠኛ ፎርሜሽኖች በእግርኳስ ውስጥ ያላቸውን ዋጋ አጋና (ክብደት ሰጥታ) ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ። ምክንያቱም በእግርኳስ ጨዋታ ላይ ውስጣዊ ፍላጎት፣ ከፍተኛ ፍቅር፣ ጥረት፣ አዕምሯዊና አካላዊ ጥንካሬ፣ ፍጥነት፣ ጥልቅ ስሜትና ክህሎት የራሳቸው ድርሻ አላቸውና፡፡ ይሁን እንጂ በሌሎች የሙያ ዘርፎች አልያም ትምህርቶች ላይ እንዳለው ሁሉ እነዚህን እሴቶች የሚደግፉ ኅልዮታዊ አቅጣጫዎችም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። እንግሊዛውያኑ ግን በእግርኳስ ረቂቅ ጉዳዮች ላይ ለመትጋት ፍላጎት ሲያሳድሩ አይታይም።
ይህ ጉድለት ሁልጊዜ ስጋት ውስጥ ሲጥለኝ ባስተውልም ለእንግሊዝ እግርኳስ እንደ ዋነኛ ችግር ተቆጥሮ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ከየትኛውም ነገር በተለየ መልኩ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መሀል የነበረውን ጊዜ ለንጽጽር ካላቀረብን በስተቀር “የእንግሊዝ እግርኳስ ደረጃ እየወረደ ነው፡፡” የሚለው ሐሳብ አያሳምነኝም። ስቬን ዮራን ኤሪክሰን በመጨረሻ ቢፌዝባቸውም፤ ከሳቸው የቆይታ ዘመን ቀደም ባሉ ጊዜያት እንግሊዝን ለሶስት ተከታታይ ዓለም አቀፍ ወድድሮች ሩብ ፍጻሜዎች ያደረሷት አልፍ ራምሴይ ብቻ ነበሩ፡፡ የውጭ አገር ሰዎችን የመጥላት ወይም የመፍራት ስሜት የሚታይባቸው ሰዎች ከገመቱት እጅጉን ጠንካራ በነበረው ምድብ የሀገሬው ዜጋ የሆኑት የሶስቱ አናብስት አሰልጣኝ ስቲቭ ማክላረን የተመራችው እንግሊዝ ለዩሮ 2008 ውድድር ከማጣሪያው ለማለፍ የገጠማት ውድቀት የአንድ ጊዜ ክስተት አልያም የረጅም ጊዜ ውድቀት ጅማሬን ማሳያ መሆኑን ታሪክ ለወደፊቱ የሚመሰክርልን ቢሆንም በሞስኮው በተካሄደው ጨዋታ ስቲቨን ዤራርድ የሁለተኛው ግማሽ ተጀምሮ በአራተኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን ጥሩ ጎል የማስቆጠር እድል ተጠቅሞ ቡድኑ በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢፈጠር ኖሮ ምናልባትም እንግሊዛውያንን የማንቃት የማነሳሳት ስሜትን ይፈጥር ነበር፡፡ ሆኖም የተፈጠረው ክስተት ሀሳቡን በተቃራኒው የጎተተ ሆነ፡፡
ዩሯጓይን እንመልከት፤ ኦስትሪያንም እናጢን፦ ይህ ውድቀት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስኮትላንድንም እንቃኝ፤ ምንም እንኳ አምስት ሚሊየን ህዝብ ብቻ ያላት ሀገር መሆኗ የጣለባት ገደብ እየከበዳትም አሁንም ቢሆን ከአቅሟ በላይ እየጣረች ትገኛለች፡፡ ከሁሉም በላይ በህዳር 1953 የእንግሊዝን እግርኳሳዊ ልዕለ ኃያልነት ህልም ማብቂያ ደውል የተጫነው ሃንጋሪን እንይ፤ በወቅቱ ከበርካታ በስኬት ያሸበረቁ ቡድኖች መካከል በገዘፈዉ ቡድን ታላቅ የነበረውንና በህዳር 2006 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ፍሬኔክ ፑሽካሽን የያዘችው ይህች ሀገር በፊፋ የአለም አገሮች እግርኳሳዊ ደረጃ በሰንጠረዡ ከመቶዎቹ ውስጥ ላለመውጣት እስካሁንም ከፍተኛ ትግል እያደረገች መገኘቷን ስንገነዘብ ይህ ውድቀት መሆኑን እንረዳለን፡፡
በጊዜው በዌንብሌይ ስታዲየም የተከሰተው የሀንጋሪው የ6-3 አስደንጋጭ ሽንፈት በእንግሊዝ እግር አንድ ወሳኝ ታሪክ የተለወጠበት ወቅት እንዲሆን አደረገ፡፡ ይህ ሽንፈት እንግሊዛውያኑ በአህጉሪቱ ካሉ ሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው አንፃር በሜዳቸው ድል የተነሱበት የመጀመሪያው ታሪካዊ ጨዋታ ከመሆኑም በላይ ብልጫ ተወስዶባቸው የተረቱበት መንገድ በወቅቱ “እንግሊዞች ዓለምን ይመራሉ!” የሚለውን አስተሳሰብ ድምጥማጡን አጠፋ፡፡ ታላቁ ጸሀፊ ብሪያን ግላንቪልም በ<ሶከር ነመሲስ> ላይ ” ይህ የእንግሊዛውያኑ የእግርኳስ ትርክት ብስለት ባልታከለበት መንገድ የመጣ የልዕለ ኃይልነት ስሜት፣ የቅርብ ቅርቡን ብቻ አሳቢነት እና የማይረባ ራስን የመነጠል ሒደት ታሪክ ነው፡፡ በሚያሳፍር መልኩ የመከነ ተሰጥኦ፣ ብርቱ በራስ የመርካት ዝንባሌ፣ መጠነ ሰፊና ግላዊነት የሚንፀባረቅበት እንዲሁም ትክክለኛ ያልሆነ አቅምን የመገንዘብ ሒደት የተቃኘ ታሪክ ነው፡፡” ሲል ለአሰቃቂው ሽንፈት ምክንያታዊ ሐሳቡን አሰፈረ፡፡ እናም የሆነው ያ ነበር፡፡
ይህም ሁሉ ሆኖ ከአስራ ሶስት ዓመታት በኋላ እንግሊዝ የዓለም ሻምፒዮን ሆነች፡፡ ሰፊው የበላይነት ቢባክንም እንግሊዝ አሁንም በግልጽ ከኃያላኖቹ የእግር ኳስ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ብዙ የተለወጠ ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አዎ ምናልባትም ከትልልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ የምንጠፋባቸው ጊዜያትና አጋጣሚዎች አሉ፤ ፍፁም መሆን ባልነበረበት ሁኔታ በሩብ ፍጻሜዎች የምንሰናበትባቸው ወቅቶችም ተፈጥረዋል፡፡ ያም ሆኖ እንኳ እንግሊዝ የዓለም ዋንጫን አልያም የአውሮፓ ዋንጫን (ዴንማርክንና ግሪክን የመሳሰሉ ያልተለመዱ አሸናፊዎች ቢኖሩም) የማግኘት ትክክለኛ እድል ካላቸው ስምንት ወይም አስር ሀገሮች መካከል መገኘቷን ቀጥላለች፡፡ ጥያቄው “ታዲያ ለምን ይህን የመገመትና ተጠባቂነት እድል አልተጠቀምንበትም?” ነው፡፡ ምናልባት የተሻለ ውህደት ያለው የወጣቶች ስልጠና መዋቅር፣ በቴክኒክና ታክቲካዊ ስርዓቶች እድገት ላይ ያሳየነው ትኩረት፣ በፕሪምየር ሺፑ የሚጫወቱ የውጭ ተጫዋቾችን ቁጥር ገደብ ማበጀት፣ ተጫዋቾች ባላቸው ነገር በመርካት ለመሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት የሚቀንሱበትን የተለመደ ባህሪ ማስወገድ ወይም ደግሞ ሌሎች በመቶ ሊቆጠሩ የሚችሉና ሁሉን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ቀደም ብለው ሲቀርቡ የነበሩ የመፍትሄ ሀሳቦች የእንግሊዝን እግርኳሳዊ እድል ያሻሽሉ ነበር፡፡ እግርኳሳዊ ስኬት ደግሞ እርግጠኛ የሆነ ቀመርና ዘዴ የሌለው ደመና መሳይ ካባ ነው፡፡ በእግርኳስ እድል የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፤ ስለዚህም ስኬታማነት በምንም መንገድ ዋስትና ሊገኝበት የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም፤ በተለይ ደግሞ ከስድስትና ሰባት የማይበልጡ ጨዋታዎች በሚደረጉባቸው ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ፡፡
“እንግሊዝ በ1966 ያሸነፈችው የዓለም ዋንጫ ለሀገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ በረከተ-መርግም ሆኖባታል” የሚል ንድፈ ሀሳባዊ አስተሳሰብ በሰፊው እየተንሰራፋ መጥቷል፡፡ ሮብ ስቲን <ማቨሪስክ> በተሰኘው መጽሄት ላይ ዳቪድ ዳውኒንግ ደግሞ <እንግሊዞች ከጀርመን እና አርጀንቲና ጋር ያላቸው ተቀናቃኝነት> በሚለው መጽሀፉ ባሰፈሩት ሐሳብ “ያ የአልፍ ራምሴይ ስኬት የእንግሊዝን እግርኳስ እድገት ወደ ኋላ ጎትቶታል።” ብለው ይከራከራሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም ” ድሉ በሀገሪቱ የእግር ኳስ አጨዋወት መሰረታዊ ሐሳብ ላይ የአልፍ ራምሴይ መንገድ በጥሩ ሁኔታ አላማን ለማሳካትና ውጤት ለማምጣት ብቸኛው አማራጭ ነው የሚል ስር የሰደደ አረዳድ እንዲሰፍን አድርጓል፡፡” ምንም እንኳ ይህ ግንዛቤ ከራምሴይ በፊት የነበረ ቢሆንም በመሰረታዊ ሐሳቡ ያለመስማማት አዝማሚያ አላሳየም፡፡ እንደሚመስለኝ ዋነኛው ችግር አሰልጣኙ ቡድናቸውን ስኬታማ እንዲሆን ያስቻሉበት ዘዴ በእንግሊዛውያን ደጋፊዎችና አሰልጣኞች ትውልድ አስተሳሰብ ዘንድ ከሰረጸውና “ትክክለኛው የአጨዋወት መንገድ ይህ ነው፡፡” ከሚለው አተያይ ጋር የተቆራኘ ብቻ አይደለም፡፡ አንድ የአጨዋወት ስልት በሆነ የተመቻቸ ሁኔታ፣ በዘመኑ ተጫዋቾች፣ በወቅቱ የእግር ኳስ እድገት ደረጃና በሌሎችም ምክንያቶች ውጤታማ ስለነበረ ብቻ ሁሌም ይህ የአቀራረብ ዘይቤ ውጤት ያስገኛል ለማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በ1966 እንግሊዞች ጥቂት ቴክኒካዊ ክህሎት የነበራቸው ተጫዋቾችን ብቻ ይዘው እንደ ብራዚሎቹ ለመጫወት ቢሞክሩ በተጫዋቾቻቸው ግዙፍ ተክለሰውነት ታግዘው ይበልጡን አካላዊ ንክኪ ያመዘነበትን አቀራረብ በሚመርጡት ተቀናቃኝ ቡድኖች ተበልጠው ከምድባቸው ለማለፍ ይቸገሩና በዓለም ዋንጫው ውድድር ብራዚላውያኑ የደረሳቸው አይነት እጣ ይገጥማቸው ነበር፡፡ ሰር አሌክስ ፌርጉሰን፣ ቫለሪ ሌቫኖቭስኪ፣ ቢል ሻንክሌይ እና ቦሪስ አርካዲዬቭን የመሳሰሉት ለበርካታ ዓመታት ውጤታማነታቸውን ዘለቄታዊ በማድረግ የሚታወቁት አንጋፋዎቹ አሰልጣኞች ከሌሎች የሚለዩበት ዋና ባህሪ በየጊዜው ራሳቸውን ከየዘመኑ እግርኳሳዊ እድገትና ለውጥ ጋር የሚያዋድዱበትና የሚያዋህዱበት ብልሀት ነው፡፡ የተጠቀሱት አሰልጣኞች ቡድኖቻቸው እግር ኳስን በተለያዩ መንገዶች ይጫወታሉ፤ ሆኖም ነባር የማሸነፊያ ቀመራቸውን በየትኛው ጊዜ እና ሁኔታ ውስጥ መተው እንዳለባቸው እንዲሁም አዲስና ቀጣይ ድል ማስገኛ ዘዴያቸውን ለመተግበር ለሚያሳዩት ድፍረት ያላቸው የጠራ ራዕይ አሰልጣኞቹ የሚጋሩት መለያቸው ነው፡፡ <ትክክለኛ የአጨዋወት መንገድ> የሚባል ነገር አለ ብዬ አለማመኔን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ አዎ- በየጨዋታዎቹ በሚፈጠሩ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ከሚመሰረተው የጆዜ ሞውሪንሆ ቼልሲ ይልቅ ውበትን በሚያስቀድመው እግር ኳስ ስሜትን ሰቅዞ ለሚይዘውና የቅብብሎች ፍሰትን ለሚያሳየው የአርሰን ዌንገር አርሰናል የበለጠ ልሳብ እችላለሁ፤ ሆኖም ይህ የአንደኛው አቀራረብ ትክክል የሌላኛው ደግሞ ስህተት መሆኑን ማሳያ ሳይሆን ግለሰባዊ ምርጫ ነው፡፡ ንድፈ- ሐሳባዊ ጉዳዮችና ተግባራዊ ልምምዶች መስማማት እንዳለባቸው በሚገባ እረዳለሁ፡፡ በአጨዋወት ጽንሰ-ሐሳብ ጀረጃ ለሌቫኖቭስኪው ዳይናሞ ኪዬቭና ለፋቢዮ ካፔሎው ኤሲ-ሚላን ባደላም ዩኒቨርሲቲ ሆኜ የኮሌጁን ሶስተኛና ሁለተኛ ቡድኖችን በያዝኩበት የሁለት ዓመታት ቆይታዬ ይበልጡን ውጤትን የሚያስቀድም አቀራረብን እንከተል ነበር፡፡ ስለእውነቱ ከሆነ ያን ያህልም ጥሩ ሳንሆን ከተጫዋቾቻችን የተሻለውን እያገኘን ስለማሸነፈችን እንጂ ከዚያ የተሻለ ማራኪ አጨዋወትን መተግበር ስለመቻላችን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በየዓመቱ ለምናሳካው ዋንጫ በቢራ መራጨት ከሚታየው ፈንጠዚያና የድል ፌሽታ ውጪ ስለአጨዋወት ዘይቤያችን የሚጨነቅ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ምንም እንኳ ግትሮቹ ግራድግሪድስ ( ከምናባዊ ቅኝት እና ስሜት ይልቅ በመሰረታዊ እውቀት ላይ የሚመሰረቱ ሰዎች) እንደሚሉት “እግር ኳሳዊ ስኬቶች የሚመዘኑት በሚመዘገቡ ነጥቦች ብዛትና በሚገኙ ዋንጫዎች ቁጥር በመሆኑ ትክክለኛው የአጨዋወት ዘዴ ዘወትር ድል የሚያስገኘው ነው፡፡” ብሎ በቀላሉ መደምደም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከድል ጎን ለጎን አስደሳች ለሆነ ነገርም ቦታ ያስፈልጋልና፡፡ ብራዚላውያን የውጤት-እግር ኳስ እና የጥበብ-እግርኳስ የሚሉት በውበትና በጥርጣሬ መካከል ያለው ውጥረት ሁሌም የሚኖር ነው፡፡ ውጥረቱ መሰረታዊ ይዘት ያለው በመሆኑም ከስፖርት በተጨማሪ በሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ ላይም ተጽእኖ ያሳድራል፡፡
ማሸነፍ ወይስ ማራኪ ጨዋታ ማሳየት? ለዚህ ጥያቄ ተጨባጭ መልስ ለማግኘት የትኛውም አይነት ሁነት በሁለቱ የተግባራዊ እውነታና ሐሳባዊነት ጽንፎች መሀል ስለመገኘቱ ማሰብ ያን ያህል ከባድ አይሆንም፡፡ ምንልባትም አዳጋቹ ነገር ትርፍ እሴት የሚገኝበትን መለየቱ ላይ ነው፡፡ ድል አድራጊነት በተሟላ ሁኔታ ተመዛኝ ካለመሆኑም በላይ የአሸናፊነት ምክንኖቹም የጊዜና ሁኔታዎች አመቺነት ጥገኞች ናቸው፡፡ በሌላ ሀገር ከሚታዩ ደጋፊዎች አንጻር ብሪታኒያውያን እግር ኳስ ወዳዶች ከተከላካይ መስመር የሚጀምር እና የሰከነ የኳስ ምስረታ ሒደት በቶሎ ይሰለቻቸዋል፡፡ ከብሪታንያውያን ተፃራሪ የሆነ ምሳሌ ለማንሳት ያህልም በካፔሎ የማድሪድ የመጀመሪያ ቆይታ ዘመን የመሃል ተከላካዩ ፈርናንዶ ሂየሮ ለግራ መስመር ተጣማሪው ሮቤርቶ ካርሎስ በፍጥነት እንዲሮጥ የሚያስችለውን የተሳካ ረጅም ቅብብል ሲከውንለት በስታዲየሙ የነበሩ የክለቡ ደጋፊዎች በጋራ ሆነው ወዲያውኑ በመጮህ ሒደቱን ተቃውመውታል፡፡
በዘመናዊ እግር ኳስ ምልከታ ሲቃኝ የቀድሞዎቹ አማተር እግር ኳሰኞች የቅርብ ርቀት ቅብብሎችን ከጀብደኝነት የራቀ ተግባር እንደሆነ የነበራቸው አስተሳሰብና አሉታዊ ትርጉም ግራ አጋቢ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በእውነቱ በሌሎች የእግርኳስ ሀገራት ለተለመደውና ምናልባትም በመጪዎቹ ጊዜያት በሀገሪቱ ሊከሰት ለሚችለው ሆን ብሎ መውደቅ እንግሊዛውያን የሚያሳዩት ጥላቻ የማይረባ ገራገርነት ይመስላል፡፡ እግር ኳስ በቀላሉ ስለማሸነፍ ብቻ እንዳልሆነ ቢታሰብም ፍጹም የድልን ወይም የአሸናፊነትን ፋይዳ እንድንክድ አያደርገንም፡፡ አልፎ አልፎ ዌንገር ለረባውም ላልረባውም አላስፈለጊ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፤ ይሁን እንጂ በ2005ቱ የኤፍ ኤ ዋንጫ ፍጻሜ ላይ የተጠቀሙበት ያልተለመደና አሉታዊ የታክቲክ አቀራረባቸው አንዳንድ ጊዜ የማሸነፍን አስፈላጊነት እንደሚያምኑበት አሳብቆባቸዋል፡፡ አልፍ ራምሴይን በአገሪቱ ታሪክ ብቸኛውን ዓለማቀፋዊ ድል አስመዝግበው መውቀስ የእንግሊዝ ደጋፊዎች የማይችሉት ቅንጦት ይሆንባቸዋል፡፡ ለታክቲካዊ ብልህነቱ እውቅና ከመቸር ይልቅም የእንግሊዝ እግር ኳስን አክስሯል ብሎ መክሰስም የተሻለ ያለመስራት ችኮነት መገለጫ ነው፡፡
በእርግጥ የሁሉንም ወገኖች ሀሳብ ዋጋ የሌለው ነው እያልኩ ባይሆንም በዋና ዋና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ስለሚታዩ የቡድኖች አቋም በብዛት ማንበብና በጥልቀት መመራመር አላስፈላጊና አደገኛ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በዓለም ደረጃ በእግር ኳሱ ዘርፍ ልዩ ብቃት የሚያሳይ ቡድን የሚታየው ከስንት አንዴ ነው፤ እንዲህ አይነቶቹ ቡድኖችም በትልልቅ ውድድሮች አሸናፊ የሚሆኑባቸው ወቅቶች ጥቂት ናቸው፡፡ የ2002ቱ የብራዚል ቡድን ይህን ሐሳብ ማጠናከሪያ ሁነኛ ማሳያ ይሆናል። ያለምንም እቅድ ከላይ ከላዩ ብቻ የተገነባውና ተቀናቃኞቹን ያልፋል ተብሎ ያልተጠበቀው ቡድን እጅግ ልዩ ነበር፡፡ በወቅቱ በማጣሪያው ያሳዩት ልፍስፍስ አቋም ተደምሮ ልዕልና የተለመደ ትርጉሙ እንደ ሌሎች ተከራካሪዎች በጉዳት፣ ድካም፣ ተገቢ ባልሆነ ስነ ምግባር እና በሌሎችም አሉታዊ ጉዳዮች ውህደት የሚዳከም መስሎ ሲታይ በፍጻሜው ውድድር ግን ይህ ሁሉ ነገር እጁን ሰጠ፡፡ በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ የውድድሩ ጥሩ ቡድን ነበረች፤ ሆኖም ምርጥነታቸውን ያሳዩት በፍጻሜው ጨዋታ ብቻ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ በዩሮ 2000 ከታዩት ሁሉ በትክክልም ምርጡ ቡድን የ ለ ብሉስ ነበር፤ ይሁን እንጂ በደቂቃዎች ልዩነት በጣልያኖች የሚሸነፉበትም አጋጣሚ ተፈጥሮባቸው ነበር፡፡
በእርግጥ ከምንጊዜም የዓለም ትልልቆቹ ቡድኖች ውስጥ የሚመደቡት የ1954ቱ የሀንጋሪ እና የ1974ቱ የሆላንድ ቡድኖች ሁለቱም በምዕራብ ጀርመን ተሸንፈዋል፡፡ ይህ ግጥምጥሞሽ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ በሶስተኝነት ደግሞ የ1982ቱ ብራዚል ደግሞ ያን ያህል ርቀትም አልተጓዘችም፡፡ ከ1966ቱ ውጪ የእንግሊዝ ቡድን ጥሩ አቋም የታየው በፖል ጋስኮይኝ እንባ እንዲሁም በእንግሊዝ የፍጹም ቅጣት ምት ሽንፈት ይበልጡን በሚታወሰው በ1990ው የዓለም ዋንጫ ወቅት ነበር። ከዚያ ጊዜ በኋላ የፍጹም ቅጣት ምት አሳዛኝ ተሸናፊነትና እንግሊዝ መደበኛ የሆነ የስምምነት ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ይህም የ1990ው ሽንፈት ጩኸት መነሻ እየሆነ ለሌሎች ውድቀቶች አጋዥ ሰበብን ፈጠረ፡፡ ለነገሩ እንግሊዞች ለውድድሩ ያደረጉት ዝግጅት ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም፡፡ በማጣሪያው ብዙ ፈተና ተጋርጦባቸው አሳማኝ ብቃት አላሳዩም፤ አሰልጣኝ ሰር ቦቢ ሮብሰንም በየቀኑ በህትመት ሚዲያው በሰላ ትችት እየተጠረቡ ከበሬታ ይነፈጋቸው ያዘ፤ የተለያዩ ተጫዋቾች ከህዝብ ግንኙነት ወኪሎች ጋር ንግግር እንደሚያደርጉ ሲጋለጥ የሚዲያ አባላት ከልምምድ ማዕከል እንዲባረሩ ተደረገ፡፡ ከዚያም ሁሉም ነገር በስርዓት አልበኝነት ጥላ ስር መከናወኑን ቀጠለ፡፡ ከአየርላንድ ሪፐብሊክና ከግብጽ ጋር በተደረጉት ጨዋታዎች እንግሊዞች አደገኛ ሆነው ቀረቡ፤ ከቤልጂየምና ካሜሩን ጋር ደግሞ እድል ከእንግሊዞቹ ጋር ሆነች፡፡ ከሆላንድና ከምዕራብ ጀርመን ጋር በተደረጉት ጨዋታዎች ድልን ባያሳኩም የሮብሰን ቡድን ጥሩ መጫወት ችሎ ነበር፡፡ በእውነቱ ከሆነ በወቅቱ እንግሊዝ በሙሉ ዘጠና ደቂቃው ያሸነፈችው ግብጽን ብቻ ነበር፡፡ ይህም ወደ መካከለኛው መደብ የእግር ኳስ አብዮት አመራ፡፡ በአንድ የሊግ ውድድር ዘመን እድል፣ የእንቅስቃሴ ጉልበት፣ ጉዳት፣ ተጫዋቾችና ዳኞች የሚፈጽሟቸው ስህተቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆን እንኳ በክረምቱ በሚደረጉትና ግፋ ቢል ሰባት በሚደርሱ ጨዋታዎች ከሚያሳድሩት ተፅእኖ ያለፈ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከአርባ በላይ ለሚሆኑ ዓመታት ምንም አይነት ዓለም አቀፋዊ ድል ሳያስመዘግብ መቆየቱ የሚያበሳጭ ነው፤ የተለያዩ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾችና ዳኞችንም የሚመለከት ኃላፊነት ሊሆን ቢችልም ከመሰረታዊ የሀገሪቱ እግር ኳሳዊ ውድቀት ጋር ግን በጭራሽ የሚነጻጸር አይሆንም፡፡ በእርግጥ በእንግሊዛውያን የጨዋታ አቀራረብ መንገዶች ላይ ህፀጾች ሊጠቀሱ ይችሉ ይሆናል፤ አዳዲስ አሰራሮችን የመቃወምና በራስ ሐሳብ ብቻ የመሄድ ስልት አላዋጣ ብሏል፤ ይሁን እንጂ በትልልቅ ዓለምአቀፋዊ ውድድሮች ላይ በሚመዘገቡ ውጤቶችን ብቻ ተገን አድርጎ የእንግሊዝ እግር ኳስ አጠቃላይ እደሳ ይሻል ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ከባድ ይመስላል፡፡
ግሎባላይዜሽን የብሔራዊ ቡድኖችን የአጨዋወት ዘይቤ እያደበዘዘው ቢገኝም በአሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፤ ተንታኞችና ደጋፊዎች አማካኝነት ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ የሚደረግ የአጨዋወት ባህል ግን ጠንካራና በቀላሉ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ሲጻፍ ግልጽ እየሆነ የመጣው ነገር ሁሉም ሀገሮች በተገቢው አኳኋን እና ፍጥነት ደራሱን ጥንካሬ እንዲለይና እንዲያውቅ በተጨማሪም የትኛውም ሀገር ሙሉ በሙሉ አምኖ የሚቀበለው አይመስልም፡፡ የብራዚላውያን እግር ኳስ በተሰጥኦና በተገኙ ነገሮች ተዘገጃጅቶ በፍጥነት መቅረብ ላይ የሚያተኩር እንዲሁም የጣልያኖቹን የመከለከል አደረጃጀት በናፍቆት የሚፈልግ ይመስላል፡፡ የጣልያናውያኑ እግርኳስም በታክቲካዊ ልህቀትና ብልሀት የተቃኘ ሆኖ የእንግሊዝ እግር ኳስ መገለጫ የሆነውን የአካል ንክኪ ድፍረት የሚያደንቅና የሚፈራ ነው፡፡ የእንግሊዝ እግር ኳስ ጉልበት፣ አካላዊ ጥንካሬና ፍጥነትን ማዕከል አድርጎ መቅረቡ መለያው ቢሆንም የብራዚሎችን ቴክኒካዊ ክህሎት እንዲኖረው ይሻል፡፡
የእግር ኳስ ታክቲኮች ታሪክ በአንድ በኩል በስነ ውበትና ውጤት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቴክኒካዊ ክህሎትና በተክለሰውነት ሁለት እርስበርሳቸው የተቆራኙ ጽንፎች ታሪክ ይመስላል፡፡ ጉዳዩን ግራ አጋቢ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በእግር ኳስ ቴክኒካዊ ችሎታ ቅድሚያ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ያደጉት ሰዎች ውጤታማ ለመሆን የጠንካራና ግዙፍ ተክለሰውነት ያላቸውን ተጫዋቾች አቀራረብ ሲሹ ወይም ወደ እነርሱ መንገድ ሲያዘነብሉ ይስተዋላል፡፡ አካላዊ ቁመና ትኩረት በሚቸረው ቦታ የነበሩት ደግሞ ተፈጥሮአዊ የቴክኒክ ብቃትን ለማዳበር ሲባዝኑ ይታያል፡፡ የእግር ኳስ ተፈጥሯዊ ውበት ካልሆነም ደጋፊዎች የሚፈልጉት የአጨዋወት ስልት ማራኪነት ደግሞ እንደ ተመልካቹ ነው፡፡ የብሪታንያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ሁሉም ባይሆኑም ምናልባት ከፍተኛ ፍልሚያ የሚታይበትን ማለትም በ2003 የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጁቬንቱስና ኤሲ ሚላን ያደረጉትን አይነት ጨዋታ ሊያደንቁ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ተመልካቾች በዋነኝነት የሚሹት ሁሉን እግር ኳሳዊ ግብዓቶች ያሟላ የፕሪምየር ሺፕን መመልከት ነው፡፡ በፕሪምየር ሺፑ የሚታየው የእግር ኳስ ተሰጥኦ ደረጃ ከአስር ዓመታት በፊት ከነበረው ሙሉ በሙሉ የተሻለ ነው ብሎ መናገር ፍትሃዊ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ከሌሎች ትልልቅ ሊጎች አንጻር ፈጣንና በኳስ ቁጥጥር ወደ ኋላ ቀረት ያለ መሆኑን ቀጥሎበታል፡፡ በ2007 እግር ኳሱን ለሌሎች አገሮች ለማስተላላፍ ከቴሌቪዥን ባለመብቶች ጋር የተደረሰውን ለሶስት ዓመት የሚቆይ የ650 ሚሊዮን ፓውንድ ስምምነት በማየት ብቻ የተቀረው ዓለም ሚዛናዊ ደስታ አግኝቷል ብሎ ይዳኛል፡፡
በ1950ዎቹ አጋማሽ የእንግሊዝ እግር ኳስ የውድቀት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ በርካታ መጻሕፍት ለህትመት ይበቁ ነበር፡፡ በኦስትሪያው ስመጥር አሰልጣኝ ሑጎ ሜይዝል ታናሽ ወንድም ዊሊ ሜይዝል የተጻፈውና <ሶኮር ሪቮሊውሽን> በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው የግላንቪል ህትመት ከሁሉም በተለየ ከፍተኛ ቁጭት የተንጸባረቀበት ነበር፡፡ እንደ አንድ እንግሊዛዊነትንና እንግሊዝ ነክ ነገሮችን እንደሚያደንቅ ታማኝ ስደተኛ የጽሁፍ ስራው ትልቅ ሀዘን ያጠላበት ነበር፡፡ ይቅርታ የማያሻውን ወግ አጥባቂ የእንግሊዛውያንን አጨዋወት ስልት ማውገዝ ለእነርሱ የኋላን ዞር ብሎ ለማየት ከማስቻሉ አንጻር ትርጉም ያለው ቢሆንም የኢምፓየሩን መጨረሻ ዘመናት ሲቆጣጠር የነበረው ተቋም ላይ እንደተሰነዘረ የደፈና ባህል ጥቃትና ተገቢ የሆነ ሚና መጫወት ያልቻሉ ሆነው ሊታይም ይችላል፡፡የእንግሊዞች አቋም መርገብገብ የእግር ኳስ ከፍታን ልዕልና ለማጣት እንደ ስህተት ይቆጠራል፡፡ግላንቪል ትክት ብሎት እንዳሰፈረው -አዎ የሆነ ጊዜ ላይ የተቀረው አለም የሚደርስበት ይሆን ነበር፡፡ ተማሪዎች ማስተርሳቸውን ይይዛሉ፤ ሆኖም በበዛ ትምክህትና ራስን አግዝፎ ከማየት ጋር የተዛመደ ከሆነ መልሶ ለውድቀት የሚዳርግ መሳሪያ ይሆናል፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው ያኔ ነው፡፡ የእንግሊዝ ከመሰረትና ምሰሶዋ የመውደቋ ጉዳይ እንደ አዲስ የሚታይ አይሆንም፡፡ መጽሀፉ የእግር ኳስ ታክቲኮችን ዝግመታዊ እድገትና ለውጥ በመመርመር አሁን ያለንበትንን ደረጃ በምን መንገድ እንደደረስንበት ለማብራራት ይሞክራል፡፡ ይህ መጽሀፍ <ሶከር ነመሲስ> እና <ሶከር ሪቮውሊሽን> በሚገኙበት ዘርፍ የሚታይ ቢሆንም ከተለየ አሁናዊ እይታ አኳያ የእንግሊዝ እግርኳስ ከወደቀበትና ይበልጡን ወደ መቀመቅ ከሚወርድበት ይልቅ ትንሳኤውን ወደሚያበስርበት እርከን የሚያሸጋግርበትን ጥርጊያ ለማሳየት ይጥራል፡፡ ለማንኛውም መጽሀፉ ታሪክ ነጋሪ እንጂ ክርክር መፍጠሪያ አይደለም፡፡
ይቀጥላል…
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
-Sunderland: A Club Transformed (2007)
-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
-The Anatomy of England (2010)
-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
-The Anatomy of Liverpool (2013)
-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)