በአዲሱ ዓመት ዋዜማ መሰረት ማኒን የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው አዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ቡድን የአንድ ተጫዋች ዝውውርን በማጠናቀቅ ያስፈረማቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች ቁጥር 17 አድርሷል።
በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚካፈለው አዲስ አበባ ወለቃ አሰፋን ነው ማስፈረም የቻለው። ዘለቃ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ስትሆን ያለፉትን ዓመታት በደደቢት አሳልፋለች።
አሰልጣኝ መሰረት ማኒ አብረዋት የሚሰሩ ረዳቶቿን መርጣ ያሳወቀች ሲሆን የሺሀረግ ለገሰ እና ሙሉጎጃም የአሰልጣኟ ረዳቶች ሆነው ስራ መጀመራቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጽያ ገልጿል።
በተያያዘ ዜና በአጠቃላይ 27 ተጫዋቾች፣ 3 አሰልጣኞች እና አንድ የህክምና ባለሙያ የያዘው አዲስ አበባ ከተማ ህዳር 1 ለሚጀመረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገውን ዝግጅት ከመስከረም 26-ጥቅምት 26 በሀዋሳ የሚያከናውን ይሆናል። ከትላንት ጀምሮም ተጫዋቾቹን ሰብስቦ ልምምድ በማድረግ ለሀዋሳው ጉዞ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል።