የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን ጥቅምት 17 እና 18 በሚደረጉ ጨዋታዎች እንደሚጀመር ይጠበቃል። አስራ ስድስቱ ተሳታፊ ክለቦችም ከነሀሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
ሶከር ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የክለቦችን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዳሰሳ ይዛላችሁ መቅረቧ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮውንም በተከታታይ ጊዜያት ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። ለዛሬ ወደ ቦዲቲ ያቀናው ቴዎድሮስ ታከለ የወላይታ ድቻን ዝግጅት ያስዳስሰናል።
በ2006 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካደገ ወዲህ በአንፃራዊ ዝቅተኛ ወጪ በርካታ ወጣት እና ከታችኛው የሊግ እርከኖች ተጫዋቾችን በማስፈረም በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ መሪነት እስካለፈው ዓመት ድረስ ቆይቷል። ድቻ የ2009 የኢትዮጵያ ዋንጫን መከላከያን በመርታት በ2010 የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ከታወቀ በኋላ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከተለመደው የዝውውር ባህላቸው ወጣ ብለው በርካታ ገንዘቦችን ፈሰስ በማድረግ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ተጫዋቾችን በማካተት ቢጀምሩም በተፈለገው ልክ ውጤት አለማስመዝገባቸውን ተከትሎ ከዘጠኝ አመታት ቆይታ በኃላ ተሰናብተው የክለቡ ከ17 ዓመት በታች አሰልጣኝ የነበሩት ዘነበ ፍሰሀን በዋና አሰልጣኝነት በመሾም ነበር የቀጠለው።
በ2010 አመዛኙን የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ የተመራው ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደካማ ውጤት በማስመዝገብ ላለመውረድ ሲታገል ቆይቶ በ30ኛው ሳምንት ወልድያን 3ለ0 በመርታት ነበር ከመውረድ የተረፈው። በአጠቃላይ በ30 ጨዋታ 8 አሸንፎ፣ 11 ተሸንፎ፣ 11 አቻ በመውጣት 25 ግብ አስቆጥሮ 27 ግብ ተቆጥሮበት በ2 የግብ ዕዳ በ35 ነጥቦች 11ኛ ደረጃን በመያዝ ለጥቂት ከመውረድ ተርፏል። በኢትዮጵያ ዋንጫ የ2009 ድሉን መድገም ሳይችል በጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ ሲሰናበት በሌላኛው ምዕራፍ ደግሞ በአፍሪካ መድረክ አስደናቂ ግስጋሴን በማድረግ በርካቶችን አስገርሟል። በቅድመ ማጣርያው ዚማሞቶን ከረታ በኃላ የግብፁ ኃያል ክለብ ዛማሌክን በደርሶ መልስ በመርታት ወደ ሁለተኛ ዙር አልፎ በታንዛኒያው ያንግ አፍሪካ ድምር ውጤት ተሸንፎ ነበር ከውድድሩ የወጣው።
ቡድኑ ለ2011 የውድድር ዘመን አዲስ መልክ ይዞ የቀረበ ይመስላል። በቅድሚያ የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀን ውል ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ያደሰው ቡድኑ ከ13 ተጫዋቾች ጋር በአቋም እና በውል መጠናቀቅ ምክንያት ተለያይቷል። በዛብህ መለዮ፣ ጃኮ አራፋት፣ አምረላህ ደልታታ፣ ተስፉ ኤልያስ፣ ኢማኑኤል ፌቮ፣ ወንድወሰን ገረመው፣ ታዲዮስ ወልዴ፣ ዮናታን ከበደ፣ ወንድሰን ቦጋለ፣ ተመስገን ዱባ፣ ዳግም በቀለ፣ ጸጋዬ ባልቻ እና ማሳማ አሴልሞ ከክለቡ ጋር የተለያዩ ተጫዋቾች ናቸው።
ክለቡ አምና ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ተጫዋቾችን መጠቀም ቢጀምርም የሰመረለት አይመስልም። ቻዳዊው ማሳማ አሴልሞ አንድም ሙሉ ጨዋታ ሳያደርግ ከክለቡ ሲለቅ ናይጄርያው ግብ ጠባቂም የወንድወሰን ገረመው ተጠባባቂ ሆኖ አሳልፏል። በአንፃራዊነት የተሻለ ጊዜ ያሳለፈው ጃኮ አራፋትም ቢሆን በተለይ በሁለተኛው ዙር በተለያዩ ምክንያቶች ብዙም ጨዋታ ማድረግ አልቻለም። ይህም ክለቡ ዘንድሮ ለውጪ ተጫዋቾች ጀርባውን እንዲሰጥ አድርጎታል።
ከክለቡ በለቀቁት ተጫዋቾች ምትክ 10 አዳዲስ ተጫዋቾች ፈርመዋል። ፍፁም ተፈሪ (አማካይ፣ ከሲዳማ ቡና)፣ አወል አብደላ (ተከላካይ፣ ከመከላከያ በድጋሚ ቡድኑን የተቀላቀለ)፣ ባዬ ገዛኸኝ (አጥቂ፣ ከሲዳማ በድጋሚ ቡድኑን የተቀላቀለ)፣ ፀጋዬ አበራ (አጥቂ፣ ከአርባምንጭ)፣ ሳሞሶን ቆልቻ (አጥቂ፣ ከጅማ አባ ጅፋር በድጋሚ የተቀላቀለ)፣ ሄኖክ ኢሳይያስ (አማካይ፣ ከጅማ አባጅፋር)፣ ታረቀኝ ጥበቡ (ቀኝ ተከላካይ፣ ከሀድያ ሆሳዕና በድጋሚ ቡድኑን የተቀላቀለ)፣ ሄኖክ አርፊጮ (ተከላካይ ከሀድያ ሆሳዕና)፣ ታሪክ ጌትነት (ግብ ጠባቂ፣ ከደደቢት)፣ መኳንንት አሸናፊ (ግብ ጠባቂ፣ ከደቡብ ፓሊስ በድጋሚ ቡድኑን የተቀላቀለ) አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ናቸው።
ወላይታ በየዓመቱ ከወጣት ቡድኑ በማሳደግ የመጫወት እድል ከሚሰጡ ቡድኖች አንዱ ሲሆን በ2010 የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ከሆነው ወጣት ቡድኑ እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ 10 ተጫዋቾችን መልምሎ በስተመጨረሻም ከ20 ዓመት ቡድኑ የመጡና ይመጥናሉ የተባሉ 5 ተጫዋቾችን ለዘንድሮ የውድድር ዓመት አሳድጓል። በዚህም መሰረት ምስክር መለሰ (አማካይ)፣ ታምራት ስላስ (አጥቂ)፣ ሀብታሙ ታፈሰ (አማካይ)፣ አቡሽ አበበ (ግብ ጠባቂ) እና ቢኒያም ገነቱ (ግብ ጠባቂ) አዲስ አዳጊዎች ናቸው፡፡
ቡድኑ ለ2011 የውድድር ዘመን ከነሀሴ 20 ጀምሮ በማድረግ ላይ ይገኛል። የሜዳውን ጨዋታ የሚያከናውንበት የሶዶ ስታድየም ዕድሳት ላይ በመሆኑም እንደ አምናው ሁሉ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ የሚገኘው በቦዲቲ ስታዲየም ነው። በአጠቃላይ 30 ተጫዋቾችን በመያዝ በጂም ውስጥ እና በሜዳ ላይ እየሰራ ሲገኝ በቀን ሁለት ጊዜ ከሚያደርገው የሜዳ ላይ ልምምድ ወደ አንድ ጊዜ በመቀነስ ዝግጅቱን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት በቡድኑ ውስጥ ስድስት ተጫዋቾች ቀላል እና ከባድ ጉዳት ገጥሟቸው እየሰሩ የማይገኙ ሲሆን ከአዲስ ፈራሚዎቹ ውስጥ ተከላካዩ አወል አብደላ እና ሄኖክ አርፊጮ ከነባሮቹ ደግሞ ከባድ ጉዳት የገጠመው ኃይማኖት ወርቁን ጨምሮ ታዳጊዎቹ ቸርነት ጉግሳ እና ውብሸት ክፍሌ በጉዳት ልምምድ ላይ አይገኙም።
ዋና አሰልጣኙ ዘነበ ፍስሀ ስለ ወላይታ ድቻ የውድድር ዓመት ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የተለየ ድቻን ይዘው ለመቅረብ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። “ለ2011 የውድድር ዘመን ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው። በአካል ብቃቱ ላይ ስንሰራ ቆይተን አሁን ደግሞ የቴክኒክ እና የቅንጅት ስራን እየሰራን ሲሆን ለ2011 ጥሩ እና የተለየውን ድቻን ይዘን ለመቅረብ እየሰራን ነው ” ያሉት አሰልጣኙ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሊጉ ላለመውረድ የታገለው ድቻ ከአምና ጉዞው ትምህርት መውሰዱን ገልፀዋል። “ባለፈው አመት ብዙ ነገሮችን አስተምሮን አልፏል። ቡድኑን ከተረከብኩ ጀምሮ ጥሩ የመነሳሳት ስሜት የነበረው ቡድን ነበር። በሊጉ እና በኮንፌዴሬሽን ውድድሩ ላይ ጥሩ ነገር አሳይቶ ነበር። ከዛ በኃላ ግን ነጥብ የመዋዠቅ ችግሮች ነበሩበት፤ ይባስ ብሎ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶም ነበር። ያ ደግሞ ዘንድሮ እንዳይኖር ተሞክሮ ወስጄ ቡድኑ እንደዛ አይነት ችግር ውስጥ እንዳይገባ ተጫዋቾቹ ስነ-ልቦና ላይ እየሰራን ነው። አሁን ላይ በቡድኑ ውስጥ የቅንጅት ስራዎችን እየሰራን ነው። ከተለያዩ ቡድኖች የመጡ አዳዲስ ተጫዋቾች ስላሉ እነዚህን ለማቀናጀት ጊዜ ያስፈልጋል። ከተለያየ ቦታ የተለያየ ነገሮችን ይዘው ስለሚመጡ ከራሴ አካሄድ ጋር በሚገባ እንዲግባቡልኝ ጥረት እያደረኩ ነው። አሁን ላይ ጥሩ እየመጡልኝ ነው። ሆኖም አሁንም የፊትነስ ችግር ያለባቸው ተጫዋቾች አሉ። ለነሱ ተጨማሪ ልምምድ እየሰጠሁ ወደነበረው አቋማቸው እንዲመለሱ እየሰራን ነው የምንገኘው። አሁን ላይ የሚታየው ነገር ጥሩ ነው። ”
እስከ አሁን ወደ ቡድኑ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ የቀላቀለው ወላይታ ድቻ ከአሁን በኃላ ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደማያመጣ የተገፀ ሲሆን አሰልጣኝ ዘነበ ስለ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች የሚከተለውን ብለዋል። ” ከሞላ ጎደል ያሰብኳቸውን ተጫዋቾት ባገኝም ወደ አራት ተጫዋቾች ግን የአዲስ አበባ ቡድኖችን ፈልገው ሄደዋል። በዕቅዴ ይዤ እንደፈለኩት ለማድረግ ባልችልም ጥሩ ኳስ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ስላሉን የተሻለ ነገር ይኖረናል። ለማምጣት ያሰብኳቸው ቢጨመሩ ደግሞ የበለጠ ጠንካራ ቡድን እንገነባ ነበር። ያም ሆኖ ከአምናው በተሻለ መልኩ ጥሩ ውጤትን ይዘን እንጨርሳለን። ሲሉ ገልፀዋል።
በቦዲቲ ከተማ ቡድኑ ልምምዱን እያደረገ ከሚገኘው ቡድን ስድሰት ተጫዋቾች (ከላይ የተገለፁ) በጉዳት ከቡድኑ ጋር ልምምድ እያደረጉ አይገኙም። ምክንያቱ ምን ይሆን ብለን ላቀረብነው ጥያቄም አሰልጣኙ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። “ለጉዳት የዳረጋቸው የልምምድ ጫና አይደለም። ከእረፍት ስለመጡ ቀለል ያሉ ነገሮችን ነበር የምንሰጣቸው። እረፍት ቆይተው ስለመጡ በአንዴ ጫና ውስጥ መክተት ጥሩ አይደለም፤ ቀስ በቀስ እየሰራኝ ከዛ በኃላ ነው ወደ ከባዱ የምንገባው። አሁን የተጎዱ ልጆች በዕርስ በዕርስ ጨዋታ በመገጫጨት የመጡ ናቸው እንጂ የልምምዱ ጫና አይደለም። ”
አሰልጣኝ ዘነበ በስተመጨረሻ በክለቡ ዙርያ የሚገኙ ሁሉ ከጎናቸው ከቆሙ የተሻለው ድቻን ይዘው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። “ይህ እግር ኳስ ነው። እግር ኳስን ስንጫወት ብቻ ሳይሆን ስንደግፍም በዕውቀት ሊሆን ይገባል። በዕውቀት ካላየነው እና ካልደገፍነው በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። እግርኳስ ደግሞ ማሸነፍ፣ መሸነፍ፣ አቻ መውጣት ያለ ነው። ስታሸንፍ ብቻ የምትደገፍ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፤ ነገ ደግሞ ስንሸነፍ ስሜታችን አንድ ሊሆን ይገባል። ለምን ሌላውም ቡድንም የሚመጣው ሊያሸንፍ ነው። ስለዚህ በዕውቀት ልንደግፍ ይገባል። ይህ ካልታከለበት በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። ምናልባት አሁንም የውጤት መዋዠቅ ሊመጣ ይችላል። ያን አስቦ ደጋፊው ሁሌም ከክለቡ ጎን ሊቆም ይገባል። አንድ ወይም ሁለት ቀን ሳይሆን ዓመት ሙሉ የምንጫወተው ስለሆነ ከጎናችን ሊሆኑ ይገባል። አዳዲስ ተጫዋቾች ተዋህደው ውጤት ለማምጣት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ልንረዳ ይገባል። ይህ ከሆነ ጥሩ ነገር ልናመጣ እንችላለን። ” ብለዋል።
ወላይታ ድቻ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመፈተሽ ይረዳው ዘንድ መስከረም 26 በሚጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የፊታችን ሀሙስ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሀሲሶ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡