ለ13ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚከናወነው የአዲስ አበባ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) በስምንት ቡድኖች መካከል ዘንድሮ ሲካሄድ የእጣ ማውጣት እና የደንብ ውይይት ስነ ስርዓቱ ነገ ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ይካሄዳል።
ከመስከረም 26 – ጥቅምት 11 በሚካሄደው ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑት ክለቦች እስከ ትላንት ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተለይታው ያልታወቁ ሲሆን አሁን ግን ከፌደሬሽኑ ባገኘነው መረጃ መሰረት በውድድሩ ላይ የሚካፈሉት ስምንቱም ክለቦች ተለይተው ታውቀዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ወላይታ ድቻ፣ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ኳራ ዩናይትድ ቀደም ብለው በውድድሩ ለመሳተፍ ማረጋገጫ መላካቸውን ተከትሎ እንደሚሳተፉ ቀድሞ የተገለፀ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳይ ግን እስከ ትላንትናው እለት በተደረጉ ድርድሮች ምላሹ ሲጠበቅ ቆይቷል። ነገር ግን ሁለቱ አካላት ባደረጉት ንግግር በጎ ምላሾች ባለመምጣታቸው ፌደሬሽኑ ተጨማሪ አማራጮችን በመመልከት ወደ ሌሎች ክለቦች ጥያቄዎችን ልኳል። በዚህም መሰረት የውበቱ አባተው ፋሲል ከነማ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍላጉት በማሳየቱ ስምንተኛው ክለብ በመሆን በሲቲ ካፕ እንደሚወዳደር ተረጋግጧል።
ከናይጄሪያ የሚመጣው ኳራ ዩናይትድ የተባለው ክለብ ነገ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገባ ሲጠበቅ ውድድሩ እስከሚጀምርበት እለት (ቅዳሜ) ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጅለት ሜዳ ልምምዶችን እንደሚሰራ ታውቋል።