የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ሪፖርት እና ዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት – ቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት እና የ2010 አፈፃፀም ሪፖርት በጁፒተር ሆቴል መከናወን ጀምሯል። ዋና ዋና ጉዳዮችን በመርሐ ግብሩ መሐል ይዘን እንቀርባለን።


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ኮ/ል ዐወል አብዱራሂም 03፡30 ሲል የጀመረውን ጉባዔ በንግግር ከፍተዋል። በንግግራቸውም አዲሱ የ2011 የውድድር ዓመት ካሳለፍናቸው ጊዜያት ከተፈጠሩ እና መልካም ተሞክሮ በሚሆኑ ነገሮች ላይ የሚተኮርበት እንደሚሆን ገልፀዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም በቀደሙት ዓመታት ያልተቃኘ እና በድድግሞሽ ያልተሞላ ይልቁኑም አዳዲስ ሀሳቦች የሚታዩበት እንደሚሆንም አብራርተዋል። ምክትል ፕሬዘዳንቱ ጨምረውም ክለቦች በራሳቸው ተነሳሽነት በተወቀሱባቸው ጉዳዮች ላይ መሻሻሎችን እንሰሚያሳዩ እና አዳዲስ አካሄዶችን ይዘው እንደሚመጡ ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል::


03:40 አቶ ከበደ ወርቁ የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ የ2010 የውድድር ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እያቀረቡ ይገኛሉ። በአቶ ከበደ ሪፖርት ውስጥ በ2010 የውድድር ዓመት የፕሪምየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ዝርዝር ውጤቶች ቀርበዋል።

03:59 በሪፖርቱ በውድድሩ የታዩ በርካታ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በቅደም ተከተል ተብራርታዋል። በመቀጠል የማሻሻያ ሀሳቦች ተጠቁመው ሪፖርቱ ተጠናቋል።

04፡00 ከመክፈቻ ንግግሩ እና ከ2010 የአፈፃፀም ሪፖርት በኋላ ጉባዔው ወደ ሻይ ዕረፍት አምርቷል።

04:05 ከዕረፍት መልስ በሪፖርቱ ላይ አጠቃላይ ውይይት ማድረግ ፣ በ2011 የሊጉ የውድድር ደንብ ላይ ማብራሪያ ማቅረብ እና የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት የማድረግ ክንውኖች ይጠበቃሉ።

04፡30 ጉባዔው ከሻይ ዕረፍት ተመልሷል።

04፡32 አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ በክለብ አመራሮች እጅ የሚገኘው የአራቱን ቋሚ ኮሚቴዎች ሪፖርት እና ከሻይ ዕረፍት በፊት በቀረበው የ2010 የውድድር ዓመት ሪፖርት ላይ የተመሰረተ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

04፡34 ኮ/ል ዳንኤል ቡሳ (ደደቢት) 

ውድድሩ ሲጀምር እና ሲጠናቀቅ እንዲሁም በመሀል የሚፈጠሩ ችግሮች ወቅቱን አዛብተዋታል። በመሆኑም የክለቦችን ሁኔታ ባላገናዘበ ሁኔታ (ለምሳሌ የሜዳ ሁኔታ )መርሀግብሩን ለማከናውን ብቻ የተደተገ ውድድር ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋርም የተያያዘ ሆኗል። አዳማ ላይም ከዛም በፊት በስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ተነጋግረናል። ነገር ግን ችግሮቹ ቀጥለዋል። አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ካልተሰጠ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ይቀጥላል። የተወሰዱት እርምጃዎችም ለውጦችን እያመጡ አይደለም። ካሁኑም ካላሰብንበት ተዘዋውሮ መጫወቱ በጣም ከባድ የሚሆን ይመስለኛል።

04፡38 አቶ መንግስቱ ሣሣሞ ( ሲዳማ ቡና )

ያለፈው ዓመት ችግር የበዛበት ነበር ነገር ግን ውድድሩን በተቻለ መጠን አካሂዶ በማጠናቀቁ ፌዴሬሽኑን አመሠግናለው። ነገር ግን ውድድሩ በየጊዜው በመራዘሙ በዚህ ዓመት ከሱፐር ሊግ የመጡ ክለቦች ከውድድር ወደ ውድድር ነው የገቡት። ይህ በራሱ ትልቅ ችግር ነው። ውድድሮች በነፃነት ያለችግር እንዲካሄዱ የተለያዩ የመንግስት አካላት እገዛ እንዲኖር ፌዴሬሽኑ መስራት ይኖርበታል። ያ ካልሆነ ግን ዘንድሮም ለውጥ ላይመጣ ይችላል።

የኮሚሽነሮች ነጥብ አሰጣጥ አልገባኝም። በራሳቸው መንፈስ ነው ነጥብ የሚሰጡት። ለምሳሌ በርካታ ቅጣት ያስተናገዱ ክለቦች አሉ በገንዘብም በቀ እና ቢጫም። እኛ ግን 16ኛ ላይ ነው የተቀመጥነው ሆኖም በሜዳችን የተቀጣ ተጨዋች የለም። ኮምሽነሮች እንደፈለጉ የተዛባ ሪፖርት ሲፅፉ ሲቀጡ አይታዩም። ስራቸው እኛንም የሚያስተምር አይደለም። ብዙ የህዝብ እና የመንግስት ገንዘብ ነው የሚፈሰው ስለሆነ የሚያስተምር ቅጣት ያስፈልጋል። 

የዚህ ዓመት ውድድር ሳይቆራረጥ መካሄድ አለበት። መቆራረጡ ክለቦች ላይ ተፅዕኖ አለው። ስለዚህ በጋራ ጥረት አድርገን መቆራረጡን ማስቀረት አለብን።

04፡47 አቶ ይትባረክ፤ ወልዋሎዓ.ዩ

የሊግ ኮሚቴ አባላት ሁሉም ዕከል ይሰራሉ ወይ ? በተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሰራ ይመስለኛል። ስለዚህ ሁሉም በስራው ይሳተፉ ወይንም የምሰሩ ሰዎች ይተኳቸው። ለምሳሌ ለወላይታ ድቻ ሄደን በፀጥታ ችግር ምክንያት ሳንጭልወት ተመልሰናል። ድቻዎች ምንም ሳይደርስብን እንድንመለስ ስላደረጉ እናመሰግናለን። ግን ከተመለስንም በኋላም ምላሽ ሚሰጠን አጥተን አዲስ አበባ 3 ቀን ቆይተን መቐለ ሄድን እንደገና ወደ አዲስ አበባ እንድንመጣ ተደርጓል። ይህ የውሳኔ አሰጣጥ ክፍተት መደገም የለበትም።

አንድ ዳኛ አንድን ክለብ በተደጋጋሚ የሚያጫውትበት ሁኔታ አለ። ይህ ለምን ይፈጠራል ? አንዳንድ ዳኞች ከሌሎች እጥፍ ጨዋታ ያጫውታሉ። ይህ ሁኔታ በደንብ መፈተሽ ይኖርበታል። እንደሊግ ኮሚቴው የዳኞች ኮሚቴ ላይም ጥቂት ሰዎች ናቸው የሚያገለግሉት። የዳኞች ብቃት ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ጋርም ስለሚገናኝ ይታሰብበት። ኮሚሽነሮችም ፃፉ የየባሉትን ነው እየፃፉ ያሉት ፌዴሬሽኑ ሊያስብበት የገባል።

በመከላከያ እና በወልዋሎ ጨዋታ የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ። እኛ ቅጣቱን ተቀብለን ወስደናል። በዳኞች እና ኮሚሽነሮች ላይ ግን እርምጃ ሳይወሰድ ጉዳዩ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ጋር ከደረሰ በኋላ በንጥልጥል ነው ያለው። ውሳኔዎች በፍጥነት መወሰን እና በአግባቡ ይፋ መደረግ አለባቸው።

የዲስፕሊን ኮሚቴ እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች ውሳኔዎች ልዩነቶች አሏቸው። ለምሳሌ የኛ ቡድን መሪ ዳኛ ተማቶ ዕድሜ ልክ ታግዷል። የቦሌ ገርጂ ቡድን መሪ ደግሞ ሁለት ዓመት ነው የተቀጣው። ይህ ከምን አንፃር ነው ? ለተመሳሳይ ጥፋት የተለያየ ቅጣት የሚወሰነው።

04፡58 አቶ አንበሴ (አዳማ ከተማ) 

እንዳካሄድ ፌዴሬሽኑ የአራቱን ኮሚቴዎች (የሊግ ፣ የዳኞች ፣ የዲስፕሊን እና የይግባኝ ሰሚ) አፈፃፀም መርምሮ ሪፖርት ቢቀርብ የተሻለ ነበር። 

የዓምና ትልቁ ችግር የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ጉዳይ ነው። አዳማ ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ሪፖርቱ ይህ ችግር በውድድሮች ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ መግለፅ ነበረበት። አሁንስ በዚህ ረገድ ምን ታስቧል ? ምን እየተሰራስ ነው ?

በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የራሳቸውን ስራ የሚሰሩ ክለቦች አሉ። ይህ ደግሞ በይፋ ታውቆ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን የሚያስችል አሰራር እንዲኖር የታሰበ ነገር አለ ወይ ?

ሌላው የሜዳ ችግር ነው። በተለይ መጨረሻ አካባቢ ለክለቦች እና ለተጨዋቾች በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።  የአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም ስራ ላይ ባለመሆኑም ጭምር ችግሩ ተፈጥሯል። ይህ ችግር ዘንድሮም እንዳይቀጥል ያሰጋል። ለመቅረፍ ምን ሊደረግ ይገባል ?

በ2010 በታዳጊዎች ዙሪያ በትክልል እየሰራ ያለው ክለቡ የቱ ነው የሚለውን የሚያመላክት ሪፖርት መቅረብ አለበት። ምክንያቱም ብዙ የሚቀሩን ነገሮች እንዳሉ ስለሚታወቅ። በተጨማሪ U17 ውሳኔ በክልል ፌዴሬሽኖች እንዲካሄዱ ተወስኗል። ውሳኔው ድንገተኛ እና እኛም ያልተማከርንበት ነው። 

የተጨዋቾች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ ነው። የደሞዝ ክፍያም እንደዛው እየጨመረ ነው። መመሪያው ሁሉም ስፖርተኛ ከደሞዙ ላይ ግብር እንዲከፍልም ያዛል። ግን አሁንም ከደሞዝ በፊት ቅድመ ክፍያዎች ይደረጋሉ። ይህ ደግሞ ክፍያዎችን ከግብር ውጪ ያደርጋል። ስለዚህ የክለቦች ያሰራር ሁኔታዎች እንዲፈተሹ ለሚንስትር መስራ ቤቱ አሳውቆ ፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ቢፃፍለትም እስካሁን የተተገበረ ነገር የለም። ከዚህ አንፃር ምን እየተሰራ ነው ?

05፡10 አቶ ጣሀ (ሀዋሳ ከተማ)

የቀረበዊ ሪፖርት ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ነገር ግን ሁለት ነጥቦችን ማንሳት ፈልጋለው። አንዱ በዲስፕሊን ጉዳይ በቂ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም። ሁለተኛ በተጨዋቾች ዝውውር ዙሪያ ከፌዴሬሽኑ በላይ ክለቦች መወቀስ አለባቸው። ለተጨዋች ገንዘብ ቀጥታ ላለመስጠት ሲባል በደጋፊ ማህበሮች በኩል ሁላ ይሰጣል። መንግስትም ከተጨዋቹ ማግኘት ያለበትን ጥቅም እያገኘ አይደለም። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ይህን ጉዳይ ቢያጤነው። 

በዲስፕሊን ጉዳይ ያልተነካካ ጉዳይ የለም። ሁሉም ተበደልኩ ብሎ ከዛም በዳይ ይሆናል። ውሳኔዎችም ክለቦችን ከክለቦች ያበላልጣሉ።

ፕሮግራም አውጣጡ እንደተፈለገ የሚወጣ ነው። መስተካከል እና የክለቦችን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መውጣት አለበት። ለምሳሌ ቡድናችን አራት አምስት ቀን ልምምድ ሳያደርግ ከቡና ጋር እንዲጫወት ተደርጓል። ይህ ቡናን እንዲጠቀም አድርጓል።

05፡16 ከባህር ዳር ከተማ

የውድድሮች ለውጥ ለክለቦች ሳይገለፅ እየቀረ ደጋፊዎች እና ክለቦች ለእንግልት ተዳርገዋል። በሪፖርቱ ይህ በተደጋጋሚ የተደጋጋሚ በመፈጠሩ ምን ትምህርት እንደተወሰደበት በሪፖርቱ አልተገለፀም።

ከፍተኛ ሊግ ውድድር ጨርሰን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ ውድድር እንድንገባ እየተደረግን ነው። ስለዚህም ፕሮግራም ከመውጣቱ በፊት መታሰብ አለበት። ልታነጋግሩን ይገባል። የሚወጣው ፕሮግራም ሶሱን አዲስ ክለቦች ታሳቢ ያድርግ።

05፡22 አቶ በያን ኢትዮጵያ ቡና 

በሀዋሳው ጨዋታ የቀረበው ክስ ልክ አይደለም። እኩል ነው ውሳኔውን የሰማነው። ለኛ አድሎ እንደተደረገ ተደርጎ መቅረብ የለበትም። እኛም ሀዋሳ ቁጭ ብለን ብዙ ወጪ አውጥተናል።

05፡23 ኮ/ር ዳንኤል ደቡብ ፖሊስ

ለሊጉ አዲስ ስለሆንን ከሌላው ዕኩል መታየት አለብን። ቅድም በባህር ዳር በኩል ተነስቷል። ነሀሴ 29 ውድድር ጨርሰን አሁን ምን አይነት ዝግጅት እንድናደርግ ነው የሚጠበቀው። ዕረፍት ለመስጠትም አዳዲስ ተጨዋቼችንም ለማስፈረም ጊዜው በቂ አይደለም። 

አዳዲስ ፊት ይዘን የምንመጣው እኛ አዳዲስ ክለቦች ነን። ለምሳሌ እኛ ጌታነህን አበርክተናል። አሁን ግን ያን ለማድረግ በቂ ጊዜ የለንም። ሊታሰብበት ይገባል።

ፌዴሬሽን ፅ/ቤቱ የፋክስ አገልግሎቱ ተቋርጧል። ይህ ለግንኙነታችን እንቅፋት ሆኗል። ልታስቡበት ይገባል።

የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እንዲባባስ የሚያደርገው የሚሰጡ ውሳኔዎች ናቸው። ውሳኔዎች በጥልቅ መታየት አለበት።

05:30 ቋሚ ኮሚቴዎች በሚመለከቷቸቅ ቅጉዳዮች ላይ ምላሽ ይሰጣሉ።

05:32 የዳኞች ተወካይ 

በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል። ወደዚህ ኃላፊነት ከመጣን 15 ቀናችን ነው። ሀሳቦቻችሁን እንደግብዐት እንወስዳለን። የመጀመሪያ ስራችንም የፊፋ ኮድስ ነበር። ከፍተኛ ችግር በዳኞች እና በክለቦች መሀል የሚፈጥረው የህግ ግንዛቤ ችግር ነው። በዚህ ዙሪያ የአንድ ቀን ፕሮግራም ያዙልን አደራ። ኢንስትራክተሮችን እንልካለን ስልጠናም እንሰጣለን። በዚህ መልኩ የህግ ክፍተቱን እናጠባለን። እኛ ሙሉ ጊዜያችንን መስዋዕት አድርገን እናንተን እናገለግላለን። ተባብረን እንስራ።

05፡36 ሚካኤል አርዓያ (ከዳኞች ማኅበር)

ትናንት ገና ነው ጥሪ የተደረገለን በዚህ ላይ ቅሬታ አለን። ከውድድር ጋር በተያያዙ ዙሪያ የተነሱት ችግሮች ክለቦች ላይ ብቻ ሳይሆን እኛም ላይ ደርሰዋል።ኢኢኢኦ ተጨዋቾች ቅጣት ተቀጥተው ሳይጨርሱ ተመልሰው ይመጣሉ። ክለቦች ያነሳችሁት ነገር ልክ ሊሆን ይችላል። ዳኖች እና ኬሚሽነሮች ሁሉም ጥሩ ናቸው ልል አልችልም። ኃላፊነት በጋራ ኢመውሰድ አለብን። 

ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት ህጋዊ የሆነ የኢንሹራንስ እንዲሁም የአበል ጉዳዮች እንዲታዩልን እንፈልጋለን።

05:49 አቶ ጌታቸው የማነብርሀን (ከውድድር እና ስነ-ስርዓት)

ክለቦች በግልፅ ሀሳባችሁን ስላቀረባችሁ እናመሰግናለን። ጥሩ ግብዐትም አግኝተናል። 2010 ውጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ከናንተ ጋር ተባብረን ለመፈፀምም ሞክረናል። እናመሠግናለን። 

የኮሚሽነሮች ነጥብ አሰጣጥ ለኛም አስቸጋሪ ሆኗል። ብዙ ጊዜም አነጋግረናቸዋል ግን እርምጃ አልወሰድንም። በዚህ ረገድ የደረጃ ዕርከን አለመኖሩ ችግር ፈጥሮብናል። ነገር ግን በኮሚኒኬ ስለማይገለፅ እንጂ እርምጃዎች ወስደናል። ችግሩ ለክለቦች አለመግለፃችን ነው። እሱን እናስተካክላለን።

ከ17 ዓመት በታች ያሉ ተጨዋቾች በሞግዚትነት በቤተሰቦቻቸው ስር የሚተዳደሩ በመሆኑ ከወቅታዊ ችግሮች አንፃር ሀላፊነት ወስደን በዙር ማጫወቱ ከባድ ይሆናል። ወጪውም ከፍተኛ በመሆኑ ያልተቀበሉት ክለቦች ነበሩ። ከነዚህ ነገሮች አንፃር ነው ውድድሩን ወደ ክልሎች ለማውረድ የወሰነው እንጂ ማናችሁንም ለመጉዳት አይደለም። 

ኢሜይል እና ስልክም የመገናኛ መሳሪያዎች ናቸው። የኛ ብቻ ሳይሆን የክለቦችም ፋክሶች የማይሰሩ አሉ። ችግሮችን አጋነን ወደ አንድ አካል አናምጣ። ሁላችንም ጋር ችግሮች አሉ።

ፕሮግራሞች ሲቆራረጡ ለኛም ከባድ ናቸው። አንድ ፕሮግራም ሲሸጋሸግ የሁሉንም ይነካል። ሁሉንም ማስደሰት ከባድ ነው። 13 ጊዜ ሲቀየር ክለቦች ሦስቴ ጠይቀዋል። ለምሳሌ ሊጉ ሳይጀመር ሦስት ክለቦች ይራዘምልን ብለው ነበር። ወቅታዊ ችግሮችም ፕሮግራሞች እንዲቀየሩ አስገድደውናል። እኛ ውድድሮች እንዲቋረጡ አንፈልግም። 

የባህር ዳር ሀሳብ ትክክል ነው። ነገር ግን ውድድሩ መጀመሪያ ለምን ዘገየ ? ክለቦች ውድድሩ ሲጀመር ክፍያ በጊዜ አያጠናቀቁም ስለዚህ ውድድሩ ቆይቶ ይጀምራል እናም መጨረሻ ላይ ይዘገያል።

06፡14 አቶ ከበደ ወርቁ

በ2010 በፕሮግራም መቆራረጥ የመጣው አብዛኛው ችግር ከነበረው ከፀጥታ ችግር ጋር እና ከሜዳ ችግር ጋር የሚገናኝ ነው። ይሄን በጋራ መውሰድ አለብን። የአደረጃጀት ችግራችንን ቀርፈን ለመፍትሄው መስራት ይኖርብናል።

06፡19 አቶ ጳውሎስ ተሰማ – ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ

ወልዋሎ ከቦሌ ገርጂ ጋር ባነሳው ጉዳይ የፍትህ ስርዓታችን ለአንድ አይነት ጥፋት አንድ አይነት ቅጣት ለማስተላለፍ አይገደድም። የጥፋት ምክንያቶችም ይታያሉ ስለዚህ አንድ አይነት ውሳኔ መጠበቅ የለበትም።

በሌላ በኩል የህግ ክፍተቶች እና ፌዴሬሽኑ ደንቦችን አለማክበሩ እንዲሁም በፍትህ ስርዓቱ ጣልቃ የመግባት ጉዳዮች ችግር ሆነዋል።

(ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባልነት መሰናበታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ አቅርበዋል)

06፡27 ሠለሞን ገ/ሥላሴ

በስራ ህይወቴ እንደ 2010 አይነት ከባድ የውድድር ጊዜ አላየሁም። ለክለቦች እና ለፌዴሬሽኑ ምስጋና አቀርባለው በጋራ ሰርተን በማጠናቀቃችን። ነገር ግን የተፈጠሩ ችግሮችን በጋራ መካፈል እና የየራሳችንን ኃላፊነት ወስደን መስራት አለብን።

የትግራይ እና በአማራ ክለቦች መካከል በገለልተኛ ሜዳ የመጫወት ጥያቄ የመጣው ከክለቦቹ ነው። እኛም የተለያዩ ውይይቶችን አድርገናል።

በተጨዋች ዝውውር ዙሪያ የመንግስትን ግብር ማስቀረት ወንጀል ነው። ማስረጃው ካለ በቀጥታ መክሰስ ይቻላል። ስለዚህ አዳማም ማስረጃው ካለው ያምጣልን። ክለቦች ራሳችሁን ጠይቁ። የቅድመ ክፍያ ጉዳይ መረጃው ይደርሰናል። ማስረጃ ግን የለም። ሁላችሁም ለህሊናችሁ እና ለመንግስት ህግ ታማኝ ሁኑ።

በአዲሱ የውድድር ዓመት ስጋት አንፃር ምን እየተሰራ ነው ለሚለው ግን በኛ በኩል መንግስትንም አካተን የሁለቱን ክልሎች አወያይተናል። ኮሚቴም ተቋቁሟል። ደንቦችን እያወጣም ይገኛል።  በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር ውይይቶች ይደረጋሉ።

የዲስፕሊን መመሪያው ረጅም ጊዜ ወስዶ ተሻሽሎ ተዘጋጅቷል ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ በመፅሀፍ መልክ ታትሞ ለሁሉም አካላት ይደርሳል።

06፡42 አቶ ሰውነት ቢሻው

እግር ኳስ አንድነትን የሚያመጣ ትልቅ ጉዳይ ነው። በሚገባ ካልተጠቀምንበት ግን ጥፋቱ ከባድ ነው። እግር ኳሱ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለውን ማወቅ ደግሞ ተገቢ ነው። ክለቦችም ለእግር ኳስ ምን አበረከትን ብለው መጠየቅ አለባቸው። ስለተተኪዎች መፈጠር መጠየቅ ያለባቸውም ክለቦች ናቸው።

06፡ 52 አቶ ተፈራ ደንበል የዲስፕሊን ኮሚቴ አባል

ከ10 ዓመት ያላነሰ ጊዜ በዚህ ስራ ቆይተናል። ፍርድ ሲፈረድ ከጥፋቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ይታያሉ። ለአንድ አይነት ጥፋት ሁሌ አንድ አይነት ፍርድ አይሰጥም።  የወልዋሎው እና የቦሌ ገርጂው ጉዳይ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነው። እንጂ እኛ ጋር ከጀርባ የተለየ ምክንያት ኖሮ አይደለም።

07፡14 ስብሰባው ለምሳ ተበትኗል።

08:30 ከምሳ መልስ ስብሰባው ቀጥሏል።

8:57 ኮሎኔል አወል

ውይይታችን በጣም ጥሩ ነው።እንደዚህ ሰዓት ወስደን የምንወያየው ለወደፊቱ ስለሆነ በደንብ መወያየታችን ይጠቅመናል። እኔ ግን 2010 ላይ ስላልነበርኩ የምላችሁ ነገር የለም። ነገር ግን አሁን ከክለቦች ሁለት ነገሮችን እንዲልኩልን እንፈልጋለን። አንደኛ የተጨዋቾች የዝውውርን ሁኔታ በተመለከተ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከ17 ዓመት በታች በተመለከተን ነው ።በተለይ የተጨዋቾችን የዝውውር ሁኔታ በተመለከተ በደንም አስባችሁ ግብአቶችን ብትሰጡን ጥሩ ነው ይህ ደግሞ የአንደኛ ዙር ግምገማ ላይ ሃሳቦችን እንድናንሸራሽር ያደርገናል።ከ17 ዓመት በታች ያልኳችሁ ደግሞ የደርሶ መልስ ጨዋታ በዚህ ውድድር ላይ መሆን እንደሌለበት በተመለከተ ነው። እናንተ እስከ ጥቅምት 30 ሃሳባችሁን ላኩልን እኛ ተጨማሪ ጥናቶችን አድርገን ውሳኔ እንወስናለን።

ከምንም በላይ ግን አሁን ማሰብ ያለባችሁ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ነው።እኛ ህግ እና ደንቦችን እናስቀምጣለን ግን እናንተ ስታዲየሞቻችሁን ከዚህ ነገር የጠራ ማድረግ አለባችሁ።

ከህግ እና ደንቦቹ በዘለለ ከክልል ሚዲያዎች እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተባብረን በስታዲየሞቻችን ሰላም እንዲሰፍን በኛ በኩክ እናደርጋል እናንተ ግን ደጋፊዎቻችሁን በአግባቡ ማስተማር እና መገለፅ አለባችሁ።

በሊጉ ላይ በአግባቡ የዲስፕሊን ችግር የሌለበትን ክለብ በአመቱ መጨረሻ ላይ ለመሸለም አስበናል።ይህንን ሽልማት አንድ ክለብ ብቻ የሚሸለመው አደለም ሁሉም ክለቦች በዲሲፕሊን ችግር ሳይኖርባቸው ከጨረሱ ሁሉንም እንሸልማለን።

ከዚህ በተጨማሪ በስታዲየሙ የሚጫወት ቡድን ሰላም ሳይኖረው ጨዋታውን የሚጨርስ ከሆነ እና ረብሻዎች በሜዳው የሚነሱ ከሆነ ሶስት ነጥብ ከሜዳው ይዞ እንዳይወጥ የሚያደርግ ህግ እናወጣለን።

የሜዳ ገቢን በተመለከተ የአዲስ አበባ ክለቦች በፐርሰንት ከፌደሬሽኑ ስለሚወስዱ ገንዘቡን በሁለት አልያም ሶስት ቀናት ውስጥ ገቢ እንዲደረግላቸው እናደርጋለን።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን እኛ ለዚህኛው አመት ብቻ ነው የምንመራው ከቀጣይ አመት ጀምሮ እንደምትረከቡን ባለፈው ተነጋግረናል ስለዚህ ለዚህ ተዘጋጁ ግን ለዘንድሮ አመት ለሊጉ አሸናፊ የሚሰጠውን ሽልማት ለማሳደግ እስበናል።

የሊግ መቆራረጥን በተመለከተ ሊጉ እንደ ቀደምት አመታት እንዲቆራረጥ አናደርግም ስለዚህ ባሰብነው መሰረት እስከ ሰኔ አጋማሽ ሊጉን ለማጠናቀቅ እንሞክራለን።

ስለዚህ እነዚህ የተነጋገርናቸውን ነገሮች እኛ ብቻ የምናስተካክላቸው አደሉም እናንተም አብራችሁን መስራት አለባችሁ። በሂደት ግን የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየተነጋገርን ለመፍታት እንሞክራለን።

የአማራ እና የትግራይ ክለቦችን በተመለከተ ከዚህ በኋላ ሁሉም የሁለቱ ክልል ክለቦች በየሜዳቸው ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ እናደርጋለን።ግን የነዚህ ክልል ክለቦች ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቅባችኋል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የሁለቱ ክልል ክለቦች እርስ በእርስ በየሜዳቸው ዬይጫወታሉ ማለት ነው።

9:35 አቶ ጳውሎስ – የይግባኝ ኮሚቴ ሰብሳቢ

ቅድም ከስራዬ ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብቼ ነበረ ነገር ግን በምሳ ሰዓት ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመነጋገሬ እና ከፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ያሉ ልዩነቶችን በመፍታቴ ለመልቀቅ ያስገባሁትን ጥያቄ አንስቻለው።

9:36 አቶ ጌታቸው የማነብርሃን 

ውድድራችን እንደ አምናው የጥሎ ማለፍ እና የሊግ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ደንቡም ከአምናው ጋር የተመሰሳሰለ ስለሆነ ብዙም ገለፃ አያስፈልገውም።

ነገር ግን ያሉ አዳዲስ ነገሮችን ለማስተዋወቅ የመጀመሪያው የፀጥታ ጉዳይ ላይ ነው ይህንን ደንብ በደንብ እዩት ከዚህ በተጨማሪ ባለሜዳ ክለቦች በሜዳችሁ ስትጫወቱ የምትቀርፁትን ቪዲዮ ለፌደሬሽኑ ማስገባት አለባችሁ። እኛ በተቻለን መጠን በአቅማችን በየስታዲየሞቹ የሚኳሄዱ ጨዋታዎችን ለመቅረፅ እንሞክራለን። ነገር ግን ይሄ በቂ ስላልሆነ የምትቀርፁትን ምስል ለፌደሬሽኑ መላክ አለባችሁ። ካልሆነ ግን በጨዋታ የሚመጡ ክሶችን ለመመርመር አዳጋች ስለሆነ ራሳችሁ ኃላፊነት ትወስዳላችሁ።

ሌላው አንድ ክለብ የሊጉ አሸናፊ ሆኖ የሚያጠናቅቅ ከሆነ እና ይሄው ክለብ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ ከሆነ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ ሳይካሄድ ይሄው ክለብ ክብሩን ይወስዳል ማለት ነው።

በአጠቃላይ ከአምናው ውድድር የተሻለ ውድድር ለማካሄድ ማሻሻያዎቹን መቀበል አለባችሁ። በተለይ ኮረኔል አወል ቅድም የጠቀሱተ የነጥብ ቅነሳው ነገር ክለቦች አፅኖት ሰታችሁ አስቡበት።

10:12 – አቶ ሰላሙ በቀለ (በ11 ድምፅ)፣ አቶ አስጨናቂ ለማ (በ11 ድምፅ) እና አቶ ሸረፋ ዴሌቾ (በ14 ድምፅ) የሊግ ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመርጠዋል።

10:18 እጣ ማውጣት ተጀምሯል

የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች

አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ

ሽረ እንዳስላሴ ከ ወላይታ ድቻ

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

ሀዋሳ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ

መቀሌ ከተማ  ከ ደደቢት 

ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ 

ደቡብ ፖሊስ ከ መከላከያ

_____________

የኢትዮጵያ ዋንጫ

ሽረ እንደስላሴ ከ ሲዳማ ቡና

አዳማ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ 

ኢትዮጵያ ቡና ከ ደደቢት

መቐለ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ

መከላከያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ፋሲል ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ