ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ከነገ ጀምሮ የሚከናወን ሲሆን ተሳታፊዎቹ ስምንት ክለቦች ተለይተው ታውቀው ትላንት የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ሆቴል መከናወኑ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በውድድሩ ሶስቱን የአዲስ አበባ ክለቦች(ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ጨምሮ አራት የክልል ተጋባዥ ክለቦችን (አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ) እና አንድ የውጪ ሀገር ክለብ ( ኳራ ዮናይትድ) በማካተት ውድድሩ እንደሚደረግ ፌደሬሽኑ መግለፁ ቢታወስም ዛሬ በተገኘ መረጃ ከሰሜኑ የአፍሪካ ክፍለ አህጉር የሚመጣው የናይጄሪያው ኳራ ዩናይትድ ከውድድሩ መሰረዙ ተሰምቷል።
ትላንት ፌደሬሽኑ የውድድሩን እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ሲያከናውን ክለቡ ከናይጄሪያ መነሳቱ ቢገሀፅም ዛሬ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለሶከር ኢትዮጵያ በገለፁት መሰረት ክለቡ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት የሚታመን መረጃ አለመላኩን ተከትሎ ውሳኔውን እንደወሰኑ አስታውቀዋል። በምድብ ሁለት ከወላይታ ድቻ፣ ፋሲል ከነማ እና ጅማ አባጂፋር ጋር ተደልድሎ የነበረው ክለቡ ባለቀ ሰዓት ከውድድሩ እንዲሰረዝ በማድረግ ባህር ዳር ከተማን በምድቡ ለማስገባት እንደተወሰነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ባህር ዳር ከተማ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚከናወን የሚጠበቀው የአማራ ከተማ ዋንጫ ላይ ይሳተፋል ተብሎ ቢጠበቅም የውድድሩ እጣ ፈንታ እስከ ዛሬ በውል ባለመታወቁ ክለቡ ጥያቄው ሲቀርብለት ለመቀበል ችሏል።
በዚህም መሰረት የክለቡ አባላት ዛሬ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ የተገለፀ ሲሆን ከነገ በስቲያ እሁድ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን ከወላይታ ድቻ ጋር ያደርጋል።