በክረምት ዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች በጊዜ ያስፈረመውና የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ውል ያራዘመው ወልዋሎ የቴክኒክ ዳይሬክተር፣ የቡድን መሪ እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ቅጥር አከናውኗል።
አቶ ስለሺ ታረቀ አዲስ የቡድኑ ዳይሬክተር ሆነው ሲሾሙ አቶ ሐብቶም አዳነ (አርማታ) ደግሞ ባለፈው ዓመት ዳኛ በመደብደብ የእድሜ ልክ እገዳ የተላለፈባቸው አቶ ማሩ ገብረፃድቅን ተክተው በቡድን መሪነት ለማገልገል ተሹመዋል። ከዚ በተጨማሪ አቶ ታደሰ አብርሃ የቡድኑ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ተደርገው ተሹመዋል። ላለፉት ዓመታት ወልዋሎን በሀኪምነት ያገለገለው ቢንያምን በመተካት አታክልቲ አለነ በቡድኑ ሀኪምነት ተሹመዋል። በቡድኑ የታዩትን ለውጦች ተከትሎ ዋናው አሰልጣኞ ፀጋዬ እና ረዳቱ ሃብቶም ኪሮስ ብቻ ለውጥ ያልተደረገባቸው ናቸው።
ከዚ ቀደም በወልዋሎ እና ደደቢት በተመሳሳይ ሙያ የሰሩት አዲሱ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታረቀ በስፖርት ሳይንስ የሁለት ዲግሪ ባለቤት መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ ትላንትና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን ስራቸው የጀመሩት ታደሰ አብርሃ ከዚ ቀደም በጉና ንግድ በግብ ጠባቂነት መጫወታቸው የሚታወስ ሲሆን ከቅጣት መልስ ቡድኑን በቡድን መሪነት በድጋሚ የተቀላቀለው ሐብቶም አዳነ በተጫዋችነት ዘመኑ ለጉና እና አዳማ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል።