የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | መከላከያ

የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ትናንት በወጣው መርሀ ግብር መሠረት ጥቅምት 17 እና 18 ይጀመራል። ሶከር ኢትዮጵያም እንደባለፈው ዓመት ሁሉ በተከታታይ የክለቦችን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ እናንተ የምታቀርብ ሲሆን ለዛሬ የመከላከያን የዝግጅት ምዕራፍ ቴዎድሮስ ታከለ የሚያስዳስሰን ይሆናል፡፡

በህዳር ወር 1938 ምስረታውን በማድረግ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በቀደምትነት ከሚጠቀሱት ክለቦች መካከል የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ አንዱ ነው። ጦር ሰራዊት በሚል ስም ጅማሮውን ያደረገው ክለቡ ከዛም በመቻል፣ ምድር ጦር፣ ፀሀይ ግባት እና መካናይዝድ በሚሉ ስያሜዎች ሲጠራ ቆይቶ በ1990ዎቹ መከላከያ የሚለውን ስያሜ በቋሚነት ከያዘ በኋላ እስካሁን በዚሁ መጠሪያ ዘልቋል። ክለቡ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከሰራዊቱ እና በስሩ ከሚገኙ የሲቪል ሰራተኞች በሚገኝ ወርሀዊ መዋጮ አማካይነት ራሱን በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

በመላከያ በ1997 ወደ ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀለ በኋላ በቅርብ ጊዜያት ሁለት ዓይነት መልክ ያለው ሲኖረው በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ለዚህም በፕሪምየር ሊጉ እና በጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ የሚያስመዘግባቸው ውጤቶችን እንደ ማመሳከሪያነት ማንሳት ይቻላል። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደጋጋሚ ወገብ ላይ እና ከዚያም በታች በመሆን በስጋት የሚጨርስባቸው ዓመታት በርከት ብለው ቢታዩም በኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ግን የሚስተካከለው አንድም ክለብ የለም። በታሪኩ 14 ጊዜያትን ዋንጫውን በማንሳት ሻምፒዮን መሆን የቻለ ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን በመሆኑ በጥሎ ማለፍ ፍፃሜ ላይ ተገናኝተው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢረታም ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቆ በአፍሪካ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችሏል። ነገር ግን በጥሎ ማለፉ ስኬታማ መሆን ቢችልም በአህጉራዊ ውድድር ላይ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በጊዜ ሲሰናበት ተመልክተናል። 

መከላከያ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሻምበል ምንያምር ፀጋዬ ዋና አሰልጣኝነት የውድድር ዓመቱን ቢጀምርም ከአሰልጣኙ ጋር መዝለቅ የቻለው ግን እስከ አጋማሹ ድረስ ብቻ ነበር። በቀጣይም አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን በመቅጥር ከነበረበት የወራጅነት ስጋት ሙሉ ለሙሉ መውጣት ባይችልም በአሰልጣኙ እየተመራ በተሳኩ ዝውውሮች ፍፁም ገብረማርያም እና ዳዊት እስጢፋኖስ የመሳሰሉ ተጨዋቾችን በማምጣት ለጥቂትም ቢሆን በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል። በ2010 በተደረጉ 30 የሊግ ጨዋታዎችም 9 አሸንፎ 8 አቻ ወጥቶ 13 ጊዜ ተሸንፎ  23 ግቦችን በተጋጣሚው መረብ ላይ በማሳረፍ 26 ግቦች  ተቆጥረውበት በ3 የግብ ዕዳ በ35 ነጥቦች 12 ደረጃን በመያዝ አጠናቋል ፡፡

ክለቡ ለዘንድሮው የ2011 የውድድር ዓመት ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር ከነሀሴ 10 ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የአየር ኃይል የልምምድ ሜዳ ዝግጅቱን ማድረግ ከጀመረ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል። አንድም የውጪ ተጫዋቾች ወደ የማያመጣው መከላከያ ካለፈው ዓመት ስብስቡ ከማራኪ ወርቁ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ የተሻ ግዛው ፣ ዐወል አብደላ ፣ ተመስገን ገ/ፃዲቅ ፣ ኡጉታ ኡዶክ፣ ፖች አደል እና ቴዎድሮስ በቀለ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ተለያይቷል። 

ከላይ በተጠቀሱት የለቀቁ ተጫዋቾች ምትክ ወደ ጦሩ የመጡት ፍሬው ሰለሞን (አማካይ ከሀዋሳ በድጋሚየተቀላቀለ) ፣ ፍቃዱ ዓለሙ (አጥቂ አዲስ አበባ ከተማ) ፣ ተመስገን ገ/ኪዳን (አጥቂ ጅማ አባጅፋር) ፣ ዳዊት ማሞ (አማካይ አዲስ አበባ ከተማ) ፣ ዓለምነህ ግርማ (ተከላካይ ወልዋሎ ዓ.ዩ) እና አበበ ጥላሁን (ተከላካይ ከሲዳማ ቡና ) ናቸው።

ባለፉት ዓመታት ከወጣት ቡድኑ በማሳደግ ተቀዛቅዞ የነበረው ክለቡ ዘንድሮ ታሪኩ (ግብ ጠባቂ) ዘሪሁን አብይ (ተከላካይ) ሰለሞን ሙላው (አማካይ ) አክሊሉ አለሙ (ተከላካይ) ኩራባቸው ቢዘልቅ (አማካይ) እና ይታጀብ ገ/ማርያም  (አማካይ) በሙከራ የዝግጅቱ አካል ያደረጋቸው ሲሆን ከመካከላቸው አንዱ ብቻ ተቀንሶ ቀሪዎቹ የዋናው ቡድን አካል እንደሚሆኑ ይጠበቃል። 


ክለቡ ለ30 የሚጠጉ ተጫዋቾችን በመያዝ ነው ለዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን አጠናክሮ የቀጠለው። ቡድኑ በቀን ሁለት ጊዜ እስከ ነሀሴ አጋማሽ ድረስ በሜዳ ላይ ልምምዱን እየሰራ የቆየ ሲሆን ከመጨረሻው የነሀሴ ወር አንስቶ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ ከሜዳ ላይ የተግባር ልምምድ ባለፈ የጂም ውስጥ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
መከላከያ ዓመቱን የስኬትን በር ሊከፍትበት የተዘጋጀበት ይመስላል። የ2010  የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ወደ ዘንድሮው ዓመት ተሸጋግሮ ሀዋሳ ላይ ሲደረግ መከላከያም በግማሽ ፍፃሜው ኢትዮጵያ ቡናን በፍፃሜው ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመርታት አሸናፊ ሆኖ በድል መንፈስ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ጅማሮ እየተጠባበቀ ይገኛል። 

ከኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ ቡድናቸው ዘንድሮ የለግ ታሪኩን እንደሚቀይር ተናግረው የነበሩት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስለ ዝግጅታቸው ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየትም ይህንን አጠናክረዋል። “ዝግጅታችንን የጀመርነው ነሀሴ 10 ነው። በሶስት ምዕራፍ የተከፈለ ዝግጅት አድርገናል። ያለፉትን 45 ቀናት ዝግጅት ከመጀመራችን በፊት ያለንን የዝግጅት ምዕራፍ ለተጨዋቾቹ በማስረዳት እንደገና ደግሞ ልጆቹ በዓመቱ ውስጥ የምንሰራውን ስራዎች መቼ ጀምረን መቼ እንደምንጨርስ ጭምር ሰጥተን በሁሉም ፌዝ ምን እንደምንሰራ አሳውቀናቸው በዛ መሰረት ቢሾፍቱ ላይ ስንዘጋጅ ቆይተናል።

 “መጀመሪያ ስናቅድም ለግማሽ ፍፃሜው ገብተናል። በዚህ ስሌት ደግሞ ውድድሩ ስንሄድ ተጨዋቾቻችንን የምናይበት እና የምናውቅበት እንደሚሆን አስበን ነበር። ውድድሩ ለዚህም ረድቶናል። አስቀድመን በቡድኑ ውስጥ ከ90% በላይ ጥሩ ሊሆኑ የሚችሉ ተጨዋቾችን አካተን የሚለቁት ለቀው ክለቡን ከነበረበት ከፍ ሊየደርጉት የሚችሉ አዳዲስ ልጆች በማምጣትም በንፈልገው ቦታ ላይ መርጠን አዘጋጅተን ነበር። ከታችም ሰባት ልጆችን አስቤ የነበረ ቢሆንም ወደ ስድስት ልጆች አምጥተን በኢትዮጵያ ዋንጫ የተሻለ ቡድን ሰርተን በመቅረብ ቡናን እና ጊዮርጊስን አሸንፈን ዋንጫውን በማንሳት እዚህ ደረጃ መድረስ ችለናል።”

 “እኔ 2010 ግማሽ ዓመት ላይ ስመጣ በዛን ወቅት ቡድኑን ማትረፍ ነበር ዕቅዴም ማድረግ የምችለውም። ያን ሁሉ እያሰብን 2011 ምን ማድረግ አለብን ስንል መከላከያ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚከፈለው ዋጋ እጀግ ትልቅ ከመሆኑ አንፃር ለምንድነው እንደእነ ጊዮርጊስ እና ቡና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለዋንጫ የማይፋለመው ብለን ከቦርድ ሀላፊዎች ጋር ጥሩ ውይይትን አድርገናል። በዚህም ለኔም ኃላፊነት ሰጥተውኝ እነሱም ከጎኔ እንደሙቆሙ ገልፀውልኝ ወደ ዝግጅት ገብተናል። በዚህ መንገድ ለመጓዝ የሁሉም አመራሮች ሚና ትልቅ ነው። የተጫዋቾቹ ስሜትም ይህንን ሚያረጋግጥ ሲሆን ውጤቱን ወደፊት የምናየው መሆኑ እንዳለ ሆኖ ለሻምፒዮንነት የሚፎካከር ቡድን እንገነባለን ” ብለዋል። በመጨረሻም አሰልጣኙ ከአሁን  በኃላ መከላከያ አዳዲስ ተጫዋቾች የማይገዛ መሆኑን እና በነባር እና አዳዲስ ተጨዋቾች በተዋቀረው ስብስባቸው ዕምነት እንዳላቸው በመናገር ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ሲጀመር ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚጫወተው መከላከያ ጥቅምት 11 ከፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋር ጋር የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ሲጠበቅ ፕሪምየር ሊጉ ጥቅምት 17 ሲጀመር ደግሞ ወደ ሀዋሳ አምርቶ አዲስ አዳጊው ደቡብ ፖሊስን የሚገጥም ይሆናል ፡፡