በትግራይ ዋንጫ የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ደደቢት እና መቐለ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸው አሸንፈዋል።
ደደቢት 1-0 ወልዋሎ ዓ.ዩ
በትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን እና ሸቶ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በጋራ በመሆን የተዘጋጀው የመጀመርያው የትግራይ ዋንጫ ውድድር ዛሬ በሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል። በ8 ሰዓት የተጀመረው የወልዋሎ እና የደደቢት ጨዋታ በሙከራዎች የታጀበ ጨዋታ ቢሆንም ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት አልነበረም። ወልዋሎዎች በመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው በመጫወት ብዙ የግብ ዕድሎችም አምክነዋል። በተለይም ሬችሞንድ ኣዶንጎ ሁለት ተጫዋቾችን አታሎ አክርሮ የመታው እና ረሺድ ሙታውሲ ያዳነበት እንዲሁም ራሱ አዶንጎ ከተመሳሳይ ቦታ መቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት ተጠቃሽ ናቸው። ቀስ በቀስ የተወሰደባቸውን ብልጫ በመመለስ በሁለቱም መስመሮች በተለይም ዳንኤል ጌድዮን በተሰለፈበት መስመር በሚሰነዝሯቸው ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ለማጥቃት የሞከሩት ደደቢቶች ብዙ የማግባት ዕድሎች ቢፈጥሩም በተጫዋቾቹ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም ዳግም አባዲ አሽምቶት ኤዶም ሄርሶውቪ በግምባሩ ገጭቶ ያመከነው እና በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አለምባንተ ካሳ አክርሮ መቶ ወደ ውጭ የወጣችበት ተጠቃሾች ሙከራዎች ናቸው።
ደደቢቶች የተከላካይ መስመራቸው ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው መጫወታቸው በብዙ ኣጋጣሚዎች ተጠቃሚ ቢያደርጋቸውም ተከላካዮቹ ከጀርባቸው ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመሸፈን ሲቸገሩ እና ከአስራት መገርሳ እና ዋለልኝ ገብሬ ለአጥቂዎች የሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ሰለባ አድርጓቸው ነበር ፤ ምንም እንኳ ወልዋሎ ኳሶቹ ተጠቅመው የረባ ሙከራ ባያረጉም። በዚህ ሁኔታ ጨዋታው በሁለቱም በኩል በሚሰነዘር ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል ሙከራዎች ተደርገዋል። በደደቢቶች በኩል ዓብዲ ዳውድ መቶት ወደ ውጭ የወጣው ይጠቀሳል። በወልዋሎ በኩልም ብርሃኑ ቦጋለ በግሩም ሁኔታ የመታው ቅጣት ምት የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ረሺድ ሙታውሲ ያዳነው እና ኤፍሬም አሻሞ ለኦዶንጎ ያሻገረለት እና ኦዶንጎ አብርዶ መቶ ረሺድ ሙታውሲ በሚያስደንቅ ብቃት ያዳናት ኳስ ይጠቀሳሉ።
ከእረፍት መልስ ደደቢት ተሽሎ የታየበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማግኘት ሲራኮቱ ቢታዩም ሁለቱም በተመሳሳይ በጥሩ ኳስ ፍሰት እና ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ክልል ሳይደርሱ ከመጀመርያው አጋማሽ ያነሰ ሙከራዎች ነበር ያደረጉት።
የጎል ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ደደቢቶች ሲሆኑ ዳንኤል ጌድዮን ከመስመር ያሻገረው ኳስ ተጠቅሞ ኤዶም ቢሞክርም ዮሀንስ ሽኩር በቀላሉ አድኗታል።
በሌላኛው የጎል ጥግ ደግሞ በድንቅ ሁኔታ ዋለልኝ ገብሬ እና ዳዊት ፍቃዱ አንድ ሁለት ተቀባብለው ዳዊት አግኝቶ አክርሮ ቢመታም ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውበታል። በዚህ እንቅስቃሴም ኦዶንጎን ቀይሮ የገባው ዳዊት ፍቃዱ በእጁ ላይ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል።
ደደቢቶች በዛሬው ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጥቅጠቅ ብለው በመከላከል እና እንደ ቡድን በጋራ በማጥቃት የተሻለ ቢንቀሳቀሱም እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጠንከር ያለ ሙከራ አላረጉም የዚህ ምክንያት ደግሞ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በአንድ መስመር ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው። በሁለተኛው አጋማሽ ዳዊት ፍቃዱ ከሞከረው ሙከራ ውጭ ብዙም ለጎል የቀረበ ሙከራ ያላረጉት ወልዋሎዎች አጨዋወታቸውን ወደ 3-4-3 ቀይረው የተሻለ የማጥቃት ዕድሎች ቢፈጥሩም ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲሸጋገር ባለው ፈጣን ያልሆነ ሽግግር ለደደቢቶች የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የተመቸ ነበር። በዚህም እንየው ካሳሁን አሻምቶት አስራት መገርሳ በግንባሩ ገጭቶ ካመከነው አስደንጋጭ ሙከራ ውጭ ይህ ነው ሚባል ሙከራ አላረገም። ሆኖም 89ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ አለምአንተ ካሳ በቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ በማስቆጠር ደደቢትን አሸናፊ አድርጓል።
መቐለ ከተማ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ
ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብዙ ጠንካራ ሙከራዎች ያልታዩበት እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በሚደረጉ ጥረቶች የታጀበ ነበር። በጥሩ የኳስ ፍሰት የጀመረው ይህ ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና መልካም ፉክክር የታየበትም ነበር። ራምኬል ሎክ ከርቀት አክርሮ መቶ ባደረገው ሙከራ ተነቃቅተው የጀመሩት ድሬዎች በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች በሙከራ በኩል የተሻሉ ነበሩ። ወሰኑ ማዜ ያሻማው ኳስ ተጠቅሞ ኢታሞኒ ካሞይኔ የመታውን እና ኦቮኖ ያዳነበት ኳስ እንዲሁም ራሱ ወሰኑ ማዜ ያሻማው የማዕዝን ምት ኃይሌ እሸቱ መቶ የአግዳሚ ብረቱ የመለሰበት በድሬ በኩል የሚያስቆጩ ሙከራዎች ናቸው።
ከጥሩ የኳስ ፍሰት ባለፈ እንደወሰዱት ብልጫ ብዙ የጎል ዕድሎች ያልፈጠሩት መቐለ ከተማዎችም ጥቂት ሚባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ጋናዊው ኦሰይ ማውሊ አሻምቶት አማኑኤል በግንባሩ ገጭቶ ያመከነው እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግራ በኩል በራሱ ጥረት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ መቶ ፍሬው ጌታሁን ያዳነበት ተጠቃሾች ናቸው። ሌላው በመቐለ በኩል ከመጀመርያው አጋማሽ ከተሞከሩት ሙከራዎች እጅግ ለጎል የቀረበው ሙከራ ኦሰይ ማውሊ ከፍሬው ሰለሞን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝንቶ ያመከናት ሙከራ ናት ፤ ማውሊ በማጥቃቱ ላይ የነበረው ኣስተዋፅኦ የላቀ ባይሆንም ተጫዋቹ ከኳስ ውጭ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የድሬዳዋ ተከላካዮች የመከላከል አደረጃጀት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲያሳርፍ እና ለሌሎች ተጫዋቾች ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ሲፈጥር ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ በመቐለ ከተማ በኩል የመሀል ሜዳ አጨዋወት ተሻሽሎ የመጣበት እና ሀይደር ሸረፋ የደመቀበት ሲሆን በድሬዳዋ በኩልም በኢታሙኒ እና ራምኬል ሎክ እየተመሩ እጅግ የተደራጀ ጫና ፈጥሮ መጫወትን (pressing) ያሳዩበት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ድሬዳዋ ከተማዎች በቆሙ ኳሶች አጠቃቀም የነበራቸው አጨዋወትም የሚበረታታ ነበር። ራምኬል ሎክ ከቅጣት ምት ባረጋት ለጎል የቀረበች ሙከራ ቢጀምርም ጎል በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን መቐለ ከተማዎች ናቸው። ቡድኑን በፍፁም ቅጣት ምት ቀዳሚ ያደረገው ደግሞ ቢያድግልኝ ኤልያስ ነው። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት መቐለ ከተማዎች ብዙም ሳይቆዩ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። በተለይም ኣሞስ አሻምቷት የድሬ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት እና ያሬድ ከበደ እና ዮናስ ገረመው ተቀባብለው ዮናስ አክርሮ መቶ ፍሬው ያዳነበት ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም እንዳለ ከበደ በሁለት አጋጣሚዎች የሞከራቸውና ፍሬው እጅግ በሚደንቅ ብቃት ያዳናቸው ሌሎች ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ናቸው። በድሬዳዋ በኩልም በርከት ያሉ ሙከራዎች ተደርገዋል። በተለይም ራምኬል ሎክ ከርቀት መቶ ወደ ላይ የወጣበት እና በሌላ አጋጣሚ ከርቀት መቶ ፍሊፔ ኦቮኖ ተፍቶ ያወጣበት ይጠቀሳሉ።
የትግራይ ክልል ዋንጫ ሰኞ ሲቀጥል 8፡00 ላይ ሽረ እንደስላሴ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ ሲጫወቱ 10፡00 ላይ መቐለ ከተማ ከ አክሱም ከተማ ይገናኛሉ።