የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ተራዝመዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዓመቱ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ጥቅምት 17 እና 18 ጀምሮ እንደሚካሄዱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ሆኖም ባሳለፍነው አርብ መስከረም 25 የሊጉ ክለቦች እና ፌዴሬሽኑ በጁፒተር ሆቴል በተደረገው የዕጣ ማውጣት ሥነ- ስርዓት ወቅት ባደረጉት ስብስባ ላይ አዲስ አዳጊዎቹ ደቡብ ፖሊስ ፣ ባህርዳር ከተማ እና ሽረ እንደስላሴ በመርሀግብሩ መጀመሪያ ቀን ላይ ቅሬታቸውን አቅርበው ነበር። ክለቦቹ በስብሰባው ላይ የአምናው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዘግይቶ በመጠናቀቁ ቡድናቸውን በዝውውሮች ለማጠናከር እና በቂ የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅትም ለማድረግ መቸገራቸውን ደጋግመው አንስተዋል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የክለቦችን ጥያቄ ከግምት በማስገባት በመጀመሪያው ሳምንት የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፉ ወስኗል።
በዚህ መሰረት ደቡብ ፖሊስ እና ሽረ እንደስላሴ በሜዳቸው መከላከያን እና ወላይታ ድቻን የሚያስተናግዱባቸው እንዲሁም ባህርዳር ከተማ አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥምበት ጨዋታዎች ወደ ፊት በሚገለፅ ቀን ላይ የሚከናወኑ ይሆናል። ይህ በመሆኑም ክለቦቹ በሁለተኛው ሳምንት የዓመቱን የመጀመሪያ ጨዋታዎቻቸውን ሲያከናውኑ ጥቅምት 24 እና 25 እንደሚደረጉ በሚጠበቁት ጨዋታዎች ደቡብ ፖሊስ ከሜዳው ውጪ ከድሬዳዋ ከተማ ሲገናኝ ባህርዳር ላይ ባህርዳር ከተማ ከሽረ እንደስላሴ ይጫወታሉ።