አጫጭር መረጃዎች በዋልያዎቹ ዙሪያ

በነገው ተጠባቂ ጨዋታ ዋዜማ ላይ ሆነን አጠቃላይ ጨዋታውን እና ዋልያዎችፕን የተመለከቱ መረጃዎችን አዘጋጅተንላችኋል

ባህርዳር ሶስተኛውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዋን ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለች ትገኛለች። ከዚህ ቀደም ዋልያዎቹ ሌሴቶን በ2017ቱ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 2-1 ሲርቱ እና ለ2016ቱ የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የነገ ተጋጣሚያቸው ኬንያን 2-0 ሲያሸንፉ ባህር ዳር በግዙፉ ዓለምአቀፍ ስታድየሟ ጨዋታዎቹን ማስተናገዷ ይታወሳል። በርካታ ደጋፊዎች ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቀውን የነገው ጨዋታም ለማስተናገድ ከተማዋ በልዩ እግር ኳሳዊ ድባብ ተሞልታ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ትላንት ሰኞ ምሽት ባረፉበትት ሆቴል የባህርዳር ከተማ ከንቲባ እና የከተማዋ ወጣቶች በተገኙበት ልዩ የራት ፣ የሽልማት እና የማነቃቂያ የባህል ፕሮግራም የተዘጋጀላቸው ሲሆን በሥነ ስርአቱ ላይም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራን ጨምሮ የስራ አስፈፃሚ አባላት ተገኝተዋል። ፕሬዘዳንቱ በግብዣው ላይ ባደረጉት ንግግር የፕሮግራሙን አዘጋጆች አመስግነው ብሔራዊ ቡድኑ መልካም ውጤት እንዲገጥመው ምኞታቸውን የገለፁ ሲሆን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱም በተመሳሳይ ምስጋና አቅርበው ፕሮግራሙ ለቡድናቸው ተጨማሪ መነቃቃት እና ጥንካሬ እንደሚሆነው ተናግረዋል።


በሌላ ዜና ነገ 10:00 ሰዓት ላይ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም የኢትዮጵያ እና የኬንያ ብሔራዊ ቡድኖች የሚገናኙበት ወሳኝ ጨዋታን በተለያዩ የስታድየሙ ክፍሎች ተገኝቶ ለመከታተል የሚጠየቀው የዋጋ ዝርዝር ይፋ ሆኗል። በዚህ መሰረትም አንደኛ ደረጃ (ክቡር ትሪቡን) 200 መቶ ብር ፣ ከክቡር ትሪቡን ግራ እና ቀኝ (ሁለተኛ ደረጃ) 50 ብር ፣ ሦስተኛ ደረጃ 25 ብር እና አራተኛ ደረጃ 10 ብር ሆኖ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል። በተያያዘ ዜና የነገው ጨዋታ በሱፕር ስፖርት 9 ኢስት ላይ በቀጥታ እንደሚተላለፍ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ምሽት 1:00 ሰዓት ላይ ቡድኑ ባረፈበት ብሉ ናይል ሆቴል እና ሪዞርት (አቫንቲ) ሆቴል ስለ ዝግጅታቸው አጠቃላይ ቆይታ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል። የጋዜጣዊ መግለጫውን አጠቃላዮ ቆይታም ምሽት ላይ የምናስነብባችሁ ይሆናል።