የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ (ኢንስትራክተር) የኬንያው አሰልጣኝ ሴባስቲያን ሚኜ ምሽት በብሉ ናይል (አቫንቲ) ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኬንያው አሰልጣኝን ቃለ መጠይቅ ቀደም ብለን ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን መግለጫ በዚህ መልክ አቅርበነዋል።
ስለ ዝግጅታቸው
ከሴራሊዮን ጨዋታ በፊት በቂ ዝግጅት አድርገን ጥሩ ውጤት አምጥተናል። ለኬንያው ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በፊት ልምምድ መጀመር ነበረብን፤ ቢሆንም ግን ካፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ክለብ በቶሎ አሳውቁ በማለቱና የጥሎ ማለፉ መርሃ ግብር መጨረስ ስለነበረበት በዛ ምክንያት ተስተጓጉለናል። ቢሆንም ግን በነበረው ጊዜ መስራት ያለብን ነገሮች ሰርተናል ።
የስነ ልቦና ዝግጅት ጥሩ ነው መነሳሳቱም የተሻለ ነው። ያም ነገር ስላለ ነው ተጫዋቾቹ ስራዬን ያቀለሉልኝ። ፍላጎት ካለ፣ መነሳሳት ካለ የመቀበል ፍላጎት ሲኖራቸው ሲነሳሱ፤ በአጭር ጊዜም የሚሰጠውን የመቀበል አቅማቸው ጥሩ ነው።
ጉዳቶች
የአስቻለውን በተመለከተ ጉዳት ከነበረባቸው አራት ተጫዋቾች አንዱ ነው። እዚህም ከመጣ በኋላ ቀለል ያለ ልምምዶችን ነበር ሲሰራ የነበረው። ያለፉትን ሶስት ቀናት ግን የዛሬውን ልምምድ ሳይጨምር የምንሰጠውን ሙሉ ልምምዶች በብቃት ሰርቷል። ከዚህ በተረፈ የህክምና ቡድኑ ነገ ጠዋት የእለቱን አሰላለፍ ከማሳወቃችን በፊት የራሳችን ውይይት ይኖረናል። እዛ ላይ የምንወስን ይሆናል፤ ግን እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በጥሩ ብቃት ላይ ነው ያለው። በኃይሉ እና ሳላህዲን በርጊቾ ግን በጉዳት ከቡድኑ ስብስብ ውጭ ሲሆኑ ለሚቀጥለው ጨዋታ ከተሻላቸው የምንጠራቸው ይሆናል። ሌላው ናትናኤል ዘግይቶ ነው ልምምም የጀመረው፤ ስለዚህ ዘግይቶ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በነበረው አቋም ላይ ተፅዕኖ አድርጎበታል። ስለዚህ እንጠቀምበታለን፤ አንጠቀምበትም የሚለውን ነገ የምናየው ይሆናል።
ስለ ኬንያ
የኬንያ ቡድን ለማሸነፍ ነው የሚመጣው። ከኬንያ-አዲስ አበባ፣ ከአዲስ-አበባ ባህር ዳር ሲመጡ ለመሸነፍ ነው የመጣነው እንደማይሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አንጠብቅምም። እኛ ደግሞ የኬንያዎች አሰልጣኝ ካላቸው የአሸናፊነት ስሜት በእጥፍ የሸናፊነት ስሜትን ይዘን ነው የምንንቀሳቀሰው። ስለዚህ አሰልጣኙ እናሸንፋለን ማለታቸው የሚገርም ነገር አይደለም።
ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች
ዘግይተው የመጡ ተጫዋቾች ቀደም ብለው እንዲመጡ ብንፈልግም ውድድር ላይ ስለነበሩ ጥለው እንዳይመጡ አድርጎቸዋል። አሁን ሲመጡ ደግሞ ለአንድ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ከቀናት በኋላ ለሚደረገው ጨዋታ ጭምር ነው የመጡት። በወጣው መርሀ ግብር መሰረት ጨርሰው ነው የመጡት። ከባድ ነገርም አልሰጠናቸውም። ሙሉ ጨዋታ ያደርጋሉ፤ ወይስ ተቀያሪ ላይ ይሆናሉ የሚለውን ነገ እንወስናለን። ዞሮ ዞሮ ለሪከቨሪ እና ፕርፎርማንስ ዋጋ እንሰጣለን።
የአካል ብቃት ደረጃ
የተጫዋቾች የአካል ብቃት ደረጃ ላይ አዲስ አበባ ላይ እንዳልኩት መጠነኛ መዘበራረቅ ነበር። በተለይም ደግሞ ጥሎ ማለፍ ላይ የነበሩ ተጫዋቾች በተሻለ የአካል ብቃት እና በተሻለ የመጫወት አቅም ላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ (ሁሉም ባይሆን) እረፍት ላይ ነበሩ። በተለይ ወርደው የነበሩት ግብ ጠባቂዎቹ ነበሩ። እነሱ ላይ ደከም ያሉ አምስት ተጫዋቾችን ጨምረን የተለየ የፊትነስ ልምምድ ፕሮግራም አዘጋጅተን ያላቸውን እና የጎደላቸውን ለሟሟላት ጥረት አድርገናል።
አቀራረብ
ከሴራሊዮን ጋር ያደረግነው አጨዋወት አሁንም እንከተላለን፤ ግን የነበረብንን ስህተቶች መቀነስ አለብን። አሁን የኬንያን አጨዋወት ተመልክተናል። ይህን ለመተግበር ጥረት እናደርጋለን። አጨዋወታችን ከሴራሊዮን የተለየ አይሆንም።
የሴራሊዮን መታገድ
አሁን ስለ ሴራሊዮን መቀጣት የምናስብበት ወቅት ላይ አደለንም። በርግጥ ውድድር ነው እኛ ከሴራለዮን የያዝነውን ነጥብ ይዘን ወደፊት ለመራመድ ባትቀጣ ይመረጣል። ነገር ግን እሱን ደግሞ ስናብሰለስል ኬንያን እንዳንረሳ አሁን ላይ ብዙ ትኩረታችን ኬንያ ላይ ነው ያለው። ሴራሊዮን ትቀጣለች አትቀጣም ስለሚለው የደረሰን ይፋዊ የሆነ ነገር የለም። ተስፋ የምናደርገው በዚህ ይቀጥላል ብለን ነው። ምናልባት ሴራሊዮን ከውድድር ብትወጣ መጎዳት ስለሌለብን የኬንያን ጨዋታ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተን እንድንገባ እና እንድንጫወት ተጫዋቻችን ላይ መነሳሳት ፈጥሯል። ይህ መሆኑ ለጨዋታው ትኩረት እንድንሰጥ አግዞናል። የሚፈጥረው የስነ ልቦና ችግር ግን የለም።
ስለ ተጋጣሚ
ኬንያ ከ ሴራሊዮን እና ጋና ጋር ያደረገቻቸው ጨዋታዎችን ምስል ተመልክተናል። በመስመር ላይ ያመዘነ አጨዋወትን እንደሚከተሉ ለማየት ችለናል። ከጋና ጋር ያደረጉት ጨዋታ ላይም የተመለከትነው ይሄን ነው። ሁለተኛ የቪዲዮ አናሊሲሱንም ወስደናል። አጨዋወታቸውን ለመመከት የሚያስችል ስራ እየሰራን ነው ያለነው፤ ሰርተንም ጨርሰናል። ነገ የምንመለከተው ይመስለኛል፡፡
በስተመጨረሻ
ሜዳው በጣም ምቹ ነው። ኳስ ለመጫወትም ሆነ ለልምምድ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። የባህርዳር ሜዳም ሽንፈት አስተናግዶ ስለማያውቅ ነገም ይደገማል ብዬ አስባለሁ። ሁሉም ግን ከጎናችን ሊሆኑ ይገባል።